‹‹በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ››
መዝ 50(51)፡7
ጥምቀት የሚለው ቃል መዘፈቅ መነከርን የሚያመለክት ሲሆን ዳግም ከውኃና ከመንፈስ የምንወለድበት የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት በሀብተ መንፈስ ቅዱስ የምንከብርበት ሥርዓት ነው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ሃይማኖትን አቅንቶ ሥርዓትን ፈጽሞ የድኅነት ሥራውን ካከናወነ በኋላ ቅዱሳን ለሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና ምድር ተሰጠኝ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› በማለት ትእዛዛዊና ሥርዓታዊ በሆነ አነጋገር ጥምቀት ለእርሱ ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑት ክርስቲያኖች ዓይነተኛ መስፈርትና መለያ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ሐዋርያው በሌላም ምንባብ ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት ሲናገር ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል›› በማለት ለመዳን ጥምቀት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ይህን ሐሳብ በተመሳሳይ ሁኔታ ጌታችን የእስራኤል ሊቅ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ባስተማረበት አንቀጽ ‹‹ዘኢተወልደ እማይ ወእመንፈስ ኢይክል በዊአ ውስተ መንግስተ እግዚአብሔር›› ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ የእግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም›› በማለት ይህንን ሐሳብ ሲያጸናው እንመለከታለን፡፡(ማር.16፡16 ፣ ዮሐ 3፡5)
‹‹የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋል›› ሮሜ 6፡7
መጠመቅ በውኑ ያድናል?
ድኅነት ማለት ሁላችንም እንደምንረዳው ለኃጢአት ምሕረት ማግኘት (remission) የሚል ፍቺ አለው፡፡ድኅነት ደግሞ ‹‹ደምም ሳይፈስ (ያለሞት) ስርየት የለም›› እንደ ተባለው የሰው ልጅም ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የዳነው ክርስቶስ ሰው በመሆኑና በእንጨት መስቀል ላያ ተሰቅሎ በደሙ ዓለምን በመቤዠቱ ነው፡፡ከዚህም ድኅነት መካፈል ለሚፈል ቅዱስ ጻውሎስ ‹‹እርሱንና የትንሳኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራውም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሳኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ›› ፊልጵስዩስ 3:10-11 ብሎ እንደተናገረ ለመዳን የጌታችንን መከራ ሞቱን ቅድስት ትንሳኤውን እንካፈል ዘንድ እንደሚገባ አበክሮ ሲናገር እናነባለን ፡፡ እንዲህ ባለው ሞትም ካልተሳተፈ በስተቀር የሰው ልጅ ድኅነትን ማግኘት አይችልም፡፡ታዲያ ይህ ሐዋርያ ሞት ሲል የሰው ልጅ ክርስቶስ ከሞተለት ሞት ውጪ ለመዳን የግድ አንገቱን ለሰይፍ ቆዳውን ለእሳት መስጠት አለበት ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ይህ ግን የአምላክን ቸርነት እና ሩኅሩኅነት የሚያዛባ ፍቺ ስለሆነ መልእክቱ እንዲህ ያለ አንድምታ የለውም፡፡ እውነተኛ የቃሉን ትርጉም ወይም ፍቺውን እራሱ ቅዱስ ጻውሎስ በሮሜ መልእክቱ ‹‹ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? … ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› በማለት ከአምላካችን ጋር በሞቱ የምንሳተፍበትና ትንሳኤውን የምንካፈልበት ጥምቀት በተባለች ደገኛ ሥርዓት እንደሆነ አስገንዞበናል(ሮሜ 6፡3-4)፡፡ቀጠል አድርጎም ‹‹ሞቱንም በሚመስል ሞት(ጥምቀት) ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን … ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን›› በማለት ደገኛ ሥርዓት በሆነች ጥምቀት አማካኝነት ከእርሱ ጋር በመሞትና በመቀበር የተጀመረው ድኅነታችን ዘላለማዊነት እንዳለውና ሥጋዊ ፈቃድ እስካላየለብን ድረስ አካላችንም ለዓለም ምኞት የሞተ ለክርስቶስ መንግስት ሕያው የሆነ እንደሆነ አስገንዝቦናል፡፡ስለዚህ በጥምቀት ድኅነት ስርየተ ኃጢአት ይገኛል ብላ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስታስተምር ከሐዋርያው ቅዱስ ጻውሎስ ቃል በመነሳት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ጥምቀት በብሉይ ኪዳን
አማናዊ ጥምቀት የሆነች የሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ከመምጣቷ በፊት በብሉይ ዘመን ለሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ብዙ ምሳሌዎች እናገኛለን፡፡ከእነዚያም ውስጥ ጥቂቶቹ እነሆ፡-
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን የደረሰውን ጥፋት ሲያነሳ ‹‹ይህ ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል›› በማለት ውኃው በጥምቀት እንደሚመሰል አስተምሯል፡፡1ኛ ጴጥሮስ 3፡21
እግዚአብሔር አብርሃም ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሆነው ተገልጦለት ‹‹ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ›› በማለት ከባረከው በኋላ በእርሱና በአብርሃም በዘሩም መካከል ያለውን ቃል ኪዳኑን ይጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ትዕዛዝና ምልክትን ሰጥቶት ነበር ዘፍ.17፡4፡፡ይኸውም ‹‹ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ የቁልፈታችሁንም ሥጋ ትገርዛላችሁ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃልኪዳን ምልክት ይሆናል› የሚል ሲሆን በዛ ጊዜ ይፈጸም የነበረው ግዝረት ለሐዲስ ኪዳኑ ጥምቀት ምሳሌ ነው(1ኛጼጥ 3፡20-21)፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሥጋንም ሰውነት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ›› በማለት ግዝረት ለጥምቀት ምሳሌ እንደነበር አስረድቷል(ቆላ 2፡11-13)፡፡እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጠውን የቃልኪዳኑን ምልክት ስለማይፈጽሙ ሰዎች ሲናገር ‹‹የቁልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቆላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገኗ ተለይታ ትጥፋ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና›› እንዳለ በተመሳሳይ ሁኔታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ሐዲሲቷ ጥምቀት በተናገረበት ክፍል በጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ስለማይወለዱ ሰዎች ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም›› በማለት ተናግሯል(ዮሐ 3፡5 ዘፍ 17፡14)፡፡
ሕዝበ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ከፈርኦን ግዛት ተላቅቀው ባሕረ ኤርትራን መሻገራቸው ሌላው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ስለዚህም ነገር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ›› ብሎ እንደተናገረው ባሕሩ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ማየ ገቦ (የጥምቀት ውኃ) ምሳሌ ሲሆን፣ ደመናውም ውኃውን ወደ ማየ ገቦ የሚለውጠው የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ፈርኦንም በክርስቶስ መስቀል ድል የተደረገው በጥምቀቱ የግዛት ደብዳቤው የተሰረዘው የዲያብሎስ ምሳሌ ነው(1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ ከመነጠቁ በፊት የዮርዳኖስን ባሕር በመጎነጸፊያው ከፍሎ አልፏል፡፡ይኸውም እስራኤለውያን ምድረ ርስትን ከመውረሳቸው በፊት ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩት መሻገር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፣ እስራኤላውያን ምድረ ርስትን ከመውረሳቸው በፊት ባሕሩን እንደተሻገሩ እስራኤል ዘነፍስ የተባልን እኛም ከመጽደቃችን ገነት መንግስተ ሰማያትን ከመውረሳችን በፊት መጠመቅ እንዳለብን ያገነዝበናል(2ኛ ነገ 2፡8) ፡፡
Fጥምቀት በመረጨት ወይስ በመዘፈቅ (በመነከር)?
ጥምቀት የሚለው ቃል ቃልበቃል ሲተረጎም መዘፈቅ መነከር ማለት ነው፡፡ከዚህም የተነሳ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አምላኳ እንዳዘዛት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ በመንከር (በመዝፈቅ) ታጠምቃለች፡፡በመንከር በመዝፈቅ ማጥመቅ እንዲያው ዘመን ያመጣው ጊዜ የወለደው ሥርዓት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ መሠረት ያለው ነው፡፡ለዚህም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት፡
· ‹ፊልጾስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቀውም ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጾስን ነጠቀው› (ሐዋ 8፡38-39) ጥምቀት በመርጨት ቢፈጸም ኖሮ ሐዋርያው ፊልጾስ ውኃውን እዚያው ጃንደረባው ያለበት ሰረገላ ድረስ አምጥቶ ያጠምቀው ነበር፡፡
· ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ›› (ቆላ 2.12) ‹‹ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› (ሮሜ 6፡4) የሚሉት እነዚህ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንደሚያስረዱን በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር መቀበራችንን የሚያመለክተን ልዩ ሥርዓት ተዘፍቀን መቀበራችን ነው! ምክንያቱም መዘፈቅ ለክርስቶስ ወደ ከርሰ መቃብር መግባት ምሳሌ ስለሆነ!
· ‹‹እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ›› (ቲቶ 3፡5) እንደተባለ አናንያም ሳውልን(ቅዱስ ጳውሎስን) ‹‹ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ›› (ሐዋ 22፡16) እንዳለው ጥምቀት ‹‹መታጠብ›› የሚል አገባባዊ ፍቺ አለው፡፡ልብስ ለማጠብ ልብሱን በውኃ ውስጥ መንከር እንደሚገባ እንዲሁ ስንጠመቅም በውኃ ውስጥ ተነክረን እንጠመቃለን፡፡(1ኛጴጥ 3፡18-21 ኤፌ 5፡26)
ጥምቀት ለድኅነታችን ዋና እና አስፈላጊ ነገር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በመረጨት መጠመቅን የምትፈቅድባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በሕክምና በጤና ጉዳይ ለመጠመቅ የማይችሉ ሕጻናትን (አዋቂም ሆኖ የሚጠመቅንም ያካትታል) ሳይጠመቁ መሞት ስለሌለባቸው በመርጨት እንዲጠመቁ ታዛለች፡፡ለምሳሌ በጤና ችግር ምክንያት በሙቀት መስጫ የሕክምና መሳሪያ ውስጥ ያለን ሕጻን ዘፍቆ ማጥመቅ አስቸጋሪና ለጤናውም አስጊ ስለሆነ በመረጨት እንዲፈጸም ታደርጋለች፡፡
F‹‹ውኃ ውስጥ መነከር ብቻ ምን ጥቅም አለው?››
Wይህን ጥያቄ በጥያቄ ብንመልሰው የተሸለ የተብራራ ይሆናል፡፡ውኃን በማፍያ ውስጥ በመጨመር ብቻ ውኃው የሚሰራው ነገር አለን? ምንም አያጠራጥርም! ውኃው ብቻውን ሊሰራው የሚችለው ነገር የለም! ነገር ግን በማፍያው ውስጥ የተጨመረው ውኃ ከባለሙያ አዕምሮ ጋር በተገናኘ ጊዜ ማሽኖችን ያንቀሳቅሳል፤ ለተለያዩ ተግባሮች ይውላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ውኃው ከኃይለ/ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ጋር በተዋሐደ ጊዜ ‹የሥላሴ ልጅነትን ያሰጣል የኃጢአት ሥርየትን ያስገኛል›፡፡ለዚህ ጥሩ አብነት አድርገን የምንጠቅሰው የሶርያ ጦር አለቃ የሆነውን የንዕማንን ታሪክ ነው፡፡ይህ ሰው ከያዘው ለምጽ እንዲፈውሰው ነቢዩ ኤልሳዕን በለመነው ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ‹‹ሂድ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ ሥጋህም ይፈወሳል አንተም ንጹሕ ትሆናለህ›› ብሎ ነገረው፡፡ንዕማንም የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ስላላወቀ ብስጭት በተሞላ ቃል ‹‹የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን?›› ብሎ ሲመልስለት ባርያዎቹ ቀርበው ‹አባት ሆይ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ ነግሮህ ቢሆን እንኳ ባደረግኸው ነበር ይልቁንስ ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ!›› ባሉት ጊዜ ከዮርዳኖድ ባሕር ገብቶ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ ሥጋውም እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆነለት፡፡ንጹሕም ሆኖ ወጣ፡፡ጌታችን ከመወለዱ ጀምሮ እውር ሆኖ የተፈጠረውንም ሰው በአፉ ምራቅ ጭቃን አርሶ አይን ካበጀለት በኋላ እንዳዘዘው በሴሎም ውኃ ተጠምቆ ነው የዳነው፡፡ስለዚህ ውኃ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲሆን እንዴት ያለ ተአምራትን እንደሚሰራ መጽሐፍ ቅዱስም ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ስለ ጥምቀት ውኃ እራሱ ፈጣሪው በተገባ ሁኔታ አስተምሮናል፡፡በውኃም እንድንጠመቅ አዞናል፡፡በአጠቃላይ የጥምቀትን ውኃ ‹ውኃ ብቻ› ብሎ መተቸት ምን ያህል ስህተት እንደሆነ በዘረዘርናቸው ማስረጃዎች መረዳት እንችላለን፡፡ (2ኛነገ 5፡13)
‹የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦሶት ናቸው› 1ኛዮሐ 5.7
F‹ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ ከሆነ የብሉይ ኪዳን አባቶች መች ተጠመቁ?›
W በብሉይ ኪዳን ጊዜ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የድኅነት ጥምቀት አልነበረም፡፡ይህ ሥርዓት የተሰራው በምጽአተ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ነው እንጂ ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል›› እንዲል ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ(ማር 16.16)፡፡ይኸውም አስቀድመን ከላይ እንደጠቀስነው ጥምቀት የምንጠመቀው የእግዚአብሔርን ልጅነት ከማግኘት ውጪ ከክርስቶስ ሞት ጋር አብሮ ለመሞት ከትንሳኤውም ጋር አብሮ ለመነሳትና ሕይወትን ለማግኘት የምንፈጽመው ሥርዓት ስለሆነ ነው፡፡ክርስቶስ ደግሞ የሞተው እንዲሁም ከሙታን ተለይቶ የተነሳው በሐዲስ ኪዳን እንጂ በብሉይ ኪዳን አይደለም፡፡ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ይጠመቁት የነበረው ጥምቀት ለሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን በሐዲስ ኪዳን የሚኖሩ ምዕመናን የሚጠመቁት ግን ከእግዚአብሔር ልጅነትን ለማግኘት ለመዳን ነው ጥምቀቱም የልጅነት የድኅነት ነው፡፡ይህ ማለት ግን በብሉይ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን አልዳኑም ማለት ሳይሆን ክርስቶስ በዕለተ አርብ ባፈሰሰው ክቡር ደሙ ተጠምቀው ድነዋል፡፡
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment