"ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ"
"እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" ፩ኛ ቆሮ. ፩፥፳፫
ክርስቶስን መስበክ ያላወቁት እንደ ክርስቶስነቱ እንዲያውቁት፣ የራቁት እንዲቀርቡ፣ የቀረቡትም እርሱን በመምሰል ወደ ቅድስና እንዲደርሱ ማገዝ ነው:: ይህንንም ባለቤቱ እግዚአብሔር “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሎ ቀድሞ በነቢያት ኋላም በሐዋርያቱ ቃል ለሕዝቡ አናግሯል ዘሌ፲፱፥፪ ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፭ :: እርሱን የመሰሉት ቅዱሳንም “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት በቃልና በሕይወት እርሱን በመምሰልና በመስበክ ሕዝቡን ወደ ቅድስና ሕይወት ይመሩታል ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩:: ቅዱሳት መጻሕፍትን ስንመለከት ክርስቶስ በብሉይ በሕግ፣ በነብያትና፣ በመዝሙራት፤ በሐዲስም በሐዋርያት ስብከት፣ በደመ ሰማዕታት፣ በሊቃውንት መምህራን ትምህርት ሲነገር ሲሰበክ እንደኖረና እንደሚኖር፤ ያልተሰበከበት ዘመንም እንደሌለ ያስረዱናል:: የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ዘመኗን ከኒህ ዘመናት ጋር አስተባብራ ክርስቶስን ስትሰብክ ኖራለች:: በታሪኳም እርሱን ያልሰበከችበት ምዕራፍ አይገኝም:: ስለሆነም ድንገት ደርሰው ክርስቶስን ለእርሷ እንግዳ አድርገው እንስበክልሽ የሚሏት አይደለችም:: ደግሞም ቤተክርስቲያን እንኳንስ ተናግራ በዝምታዋም ክርስቶስን የምትሰብክ ናት፡፡ ክርስቶስ እንኳንስ በቤተክርስቲያን በምኩራብም ተሰብኳልና፡፡
አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ቤተክርስቲያን ክርስቶስ ሳትሰብክ የቀረች ፣ ክርስቶስን ጋርዳ ቅዱሳንን፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን የምትገልጥ አይደለችም፡፡ ክርስቶስን የማትሰብክ ከሆነ ቀድሞም እርሷ የክርስቶስ ማደሪያ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ቤት፣ ቤተክርስቲያን አይደለችም፡፡ ራሷንና የቆመችበት መሠረቷንስ ትታና ዘንግታስ እንዴት ይሆናል? "አንተ ውእቱ መሲሕ ወልዱ ለእግዚአብሔር" "አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ" ማቴ ፲፮፥፲፮ በሚል ጽኑ መሠረት ላይ ታንጻለች፡፡ በዚህም ጽኑ መሠረት ላይ የተከላትና ያጸናት ደግሞ እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡
በሌላ አንጻር ደግሞ ቤተክርስቲያን ቅዱሳንን ማክበሯ እርሱ ባለቤቱ ስላከበራቸውና በቤቱም ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር መታሰቢያ ስለሰጣቸው ነው፡፡ ቤቱም ደግሞ እራሷ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ እነርሱ(ቅዱሳን) ስለ ክብሩና እርሱንም በመስበክ በዘመናቸው ሁሉ የደከሙ፣ የዚህችን ዓለም ጣዕም የናቁ፣ መራራ ሞትን የታገሱ፣ ለእርሱ እየተገዙ እርሱንም አያገለገሉና እያከበሩ "እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል" ዮሐ ፫ ፥ ፴ እያሉ የኖሩ ናቸው ኢሳ ፶፮፥፬–፯፡፡ አስቀድሞ ቤተክርስቲያን የማይገባቸውንና ለአምላካቸው የሚገባውን ክብር ለእነርሱ አትሰጥም፡፡ እነርሱም አንኳን የማይገባቸውን የሚገባቸውንም ክብር ለመቀበል አይፈቅዱም ራዕይ ፳፪ ፥ ፰–፱፡፡
ከዚህም ባሻገር የቅዱሳንን ድርሳን ገድል መንገርን ቤተክርስቲያን የተማረችው ሌላ ከማንም ሳይሆን ከእርሱ ከቅዱሳን አምላክ ከክርስቶስ ነው፡፡ ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ክብር ሲናገር ታውቋል፡፡ ማቴ. ፲፩፥፯-፲፬
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምዕመናን በጻፈላቸው ቃለ መልዕክት አንደገለፀው ቤተክርስቲያን እንደ አይሁድ ምልክትን በመሻት፣ ወይም እንደ ግሪክ ሰዎችም በዚህ ዓለም ጥበብ ሳይሆን የተሰቀለውን ክርስቶስ ትሰብካች፡፡ አዎን ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ነገረ መስቀሉን፣ ክርስቶስንም በመከተል ይቀበሉት ዘንድ ያላቸውን መከራ እያሳሰባች መስቀሉን ተሸክመው እንዲከተሉት ልጆቿን ታዘጋጃለች፡፡ በዚህች ዓለም ክርስቶስን መስለው ሲኖሩ ጽኑ መከራ፣ በብዙ መራብ፣ መራራ ሞት እንደሚጠብቃቸው ታስተምራለች:: በመስቀሉ በተፈጸመ የማዳን ሥራ ፍጹም ድኅነትን፣ በመስቀሉ በተሰጣቸው ኃይል ጸብአ አጋንንትን ድል ማድረግን፣ በመስቀሉ ሥር በተፈጸመ ሥጦታ ልመና ምልጃ የምታውቅ እናት እንደተሰጣቸው በማሰብ ከፊታቸው ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንዲፈጽሙ ትመክራለች ታስተምራለች:: ክርስትና ከቤተልሔም እስከ ዮርዳኖስና ሆሳዕና ድረስ ብቻ ሳይሆን እስከ ቀራንዮ ጐለጐታ የሚዘልቅ፣ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ሳያደርስ የማይቀር መሆኑን ታውጃለች፡፡ በመስቀሉ ዙሪያ የተገኙ እናቱንና ቅዱሳኑንም ታሳስባለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን መስበኳ እንደ አይሁድ አለማመን፣ እንደ ግሪክ ሰዎችም ሞኝነት የሚመስላቸው ቢበዙም ይህን ከማድረግ ግን ወደ ኋላ አትልም፡፡
ቤተክርስቲያን እንዴት ባለ ሁኔታ እንደምንስ ባለ ጐዳና ክርስቶስን እንደምትሰብክ የተወሰኑ ነጥቦችን በማቅረብ ለማየት እንሞክር፡፡
- በጉባዔ
ቤተክርስቲያን ክርስቶስን ከምትሰብክባቸው መንገዶች አንዱ ጉባኤ ሰርታ፣ መምህራኑን ለማስተማር አብቅታ፣ ተማሪዎቹንም ለትምህርት ጠርታ ሁሉን በአንድነት ሰብስባ የምትሰጠው ትምህርት ነው፡፡ ይህም ትምህርት ወልደ አብ በመለኮቱ ወወልደ ማርያም በትስብእቱ የሆነ ክርስቶስ ከቅድምናው /ዓለማት ከመፈጠራቸው በፊት ከነበረው መነሻ ከሌለው መጀመሪያ/ አንስታ ሰው ስለመሆኑ፣ ሰለጥምቀት፣ ስቅለቱ፣ ስለሞቱና ትንሳኤው ስለእርገቱ ዳግም ምጽአቱ መጽሐፍ እየጠቀሰች፣ ምሥጢር እያፍታታች፣ ምሳሌ እየመሰለች ልጆቿ ሊሰሙና ሊረዱ በሚችሉት መጠን ታስተምራለች፡፡ ከዚሁም ጋር አያይዛ እርሱን በማክበራቸው የከበሩ ቅዱሳንን ክብር ትነግራለች፡፡ ይህም እንደየ ትምህርት አሰጣጡ ጠባይ በቃል፣ በንባብ፣ በዜማ እየሆነ በጊዜውና በቦታው ከአዕምሮ በማይወጣ መልኩ ይቀርባል፡፡
- ምሥጢራት በመፈጸም
ቤተክርስቲያን ለልጆቿ ከምትፈጽማቸው ምሥጢራት ጥምቀት ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህ ምሥጢር ተጠማቂው የሥላሴን ልጅነት ከማግኘት ባሻገር ከክርስቶስ ጋር በሞትና በትንሳኤው ተባባሪ እንዲሆን ታደርጋለች፡፡ በጥምቀት ጊዜ በገንዳው መዘፈቅ ጌታ በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ማደሩን ሲያመለክት፤ ከመጠመቂያው ገንዳ መውጣቱ በሦስተኛው ቀን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን ያጠይቃል፡፡ ሮሜ. ፮፥፩–፯
በሌላውም ምሥጢር በምሥጢረ ቁርባን ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለልጆቿ በማቀበል (በማቁረብ) ዘላለማዊ ሕይወትን እንዲያገኙ፣ ክርስቶስ በእነርሱ እነርሱም በክርስቶስ እንዲኖሩ፣ የክርስቶስ ማደሪያዎች /ቤተመቅደስ/ እንዲሆኑ ታደርጋለች፡፡ ሰው የተመገበውን ያንኑ እንዲሸት፣ ብልቃጥም በውስጡ የያዘው ሽቶ እንዲሸት አነርሱም መዓዛ ጠረናቸው ክርስቶስ ይሆናል፡፡ በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሚሰብኩ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና" እንዲል ፪ኛ ቆሮ ፪፥፲፭፡፡ ሰዎች ማደሪያው ይሆኑ ዘንድ ከማብቃት በላይ ክርስቶስን መስበክስ ከወዴት ይገኛል?
ይህ የሚያስረዳን ሌላ ነገር ቤተክርስቲያን ልጆቿን ገና ከ40 እና ከ80 ቀናቸው ጀምራ በምሥጢራቱ ከሚያገኙት ዋጋ ባሻገር ከአምላካቸው ጋር የምታቀራርባቸው መሆኑን ጭምር ነው፡፡ ለማሳያነት እኒህ ብቻ ቀረቡ እንጂ ሌሎቹም ምሥጢራት በተለያየ መንገድ ክርስቶስን የሚሰብኩና የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ይቆየን
ይቆየን