Monday, May 2, 2011

‹‹አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን?›› ዮሐ 3÷10

እንደ አባታች ቅዱስ ያሬድ አሰያየም ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት ሲኖሩት አሁን ያለንበት ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ በመባል ይታወቃል፡፡በዚህም እለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ የተባለ የአይሁድ አለቃን ስለ ደገኛይቱ ሥርዓት ስለ ጥምቀት አምልቶ አስፍቶ ያስተማረበት ነው፡፡ይሁን እንጂ ከዚህ መልእክቱ ባለፍ የኒቆዲሞስ ሕይወቱ ብቻ ዛሬ ላይ ለምንገኝ መምህራነ ወንጌል እንዲሁም እግዚአብሔርን ለምናገለግል ሰዎች  ጉድለታችንን የምናይበት መጽሔታችን (መስታወታችን) አገልግሎታችንን የምንመዝንበት መድሎት (ሚዛን) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ስለዚህም የቃሉን መልእክት እንዲሁም ጭብጥ ሐሳቡን ለመረዳት ቃሉን ከትርጓሜው ጋር አዋሕዶ ማየት ማጤን ይገባል፡፡     
          ቃሉን የምናገኘው በዮሐ. 3 ላይ ሲሆን ከቁጥር አንድ ጀምረን ስንመለከተው ‹‹ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እም ፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ›› ‹‹ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆን ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበር››፡፡ ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ ገዢ ሲሆን ገዢነቱም ሕገ ኦሪትን የተማረ ስለነበር በትምህርቱ /በእውቀቱ/ ፣በሹመቱ እንዲሁም ባለው ሀብት በባዕለ ጸግነቱ በእነዚህ ሦስት ነገራት የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ይህም ሰው ‹አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ ይመጣ ነበር›፡፡ አስቀድሞ የሚለው ቃል ኋላ ጌታችን በቅንዓተ ሰይጣን በአይሁድ ተሰቅሎ ሲሞት ክቡር የሆነ ሥጋውን ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር ለመገነዝ ይመጣልና ቀዳሚ ምፅአቱን /መምጣቱን/ ለመናገር የተጠቀመው ቃል ነው፡፡ አንድም በመዓልት (በቀን) ከሚመጡት አስቀድሞ ይመጣ ስለነበር ይህን ለማመልከት የገባ ቃል ሲሆን ከሁሉ በላይ ግን ከሁሉ አስቀድሞ በሌሊት ይመጣ የነበረው ውዳሴ ከንቱን ሽቶ መምህር ነኝ እያለ እስከ ዛሬ ትምህርት ሳይከተትለት ኑሯል ይሉኛል ብሎ ነው፡፡ አይሁድም ‹እመቦ ዘአምነ ቦቱ ከመ ክርስቶስ ይሠደድ እምኩራብ›  እንዲል ክርስቶስን ከቤተ ምኩራባቸው ሰደው ገፍተው እንዳስወጡት በእርሱ ያመኑትን ትምህርቱንም የሰሙትን ወደ ቤተ ምኩራባቸው እንዳይገባ የሚል አዋጅ ነግረው ስለነበር ከቤተ ምኩራብ ይለዩኛል ይሰዱኛል ብሎ ስለፈራ በሌሊት እየመጣ ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ይማር ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ኒቆዲሞስ ገና ከኦሪት አለመላቀቁን በመንፈስ ቅዱስ አለመሟሟቁን ያመለክታል፡፡
          ይህ ሰው ከፈሪሳውያን ወገን እንዲሁም ሊቅ የብሉይ መምህር ቢሆንም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ያምን ነበር፡፡ የእጁንም ስራ እየተመለከተ ‹‹እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን›› በማለት አይሁድ አልገባ ያላቸውን የጌታችንን ወልደ እግዚአብሔርነት (የእግዚአብሔር ልጅነት) ጠልቆ ባይገባውም በመጠኑ ተረድቶት ነበር፡፡ ጌታችንም መልሶ “ዘኢተወልደ ዳግመ ኢይሬእያ ለመንግስተ እግዚአብሔር”  ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም›› በማለት ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔር መንግስት የሚገኝባት ሃይማኖትን አያውቃትም በማለት በመጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅነትን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ማግኘት እንዲገባ  ያስተምረው ጀመር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል› እንዳለ ከጥምቀት ማመን አይቀድምም ወይ ስለምን ጥምቀትን አስቀደመ ቢባል ‹ወአልቦ ዘይክል ብሂለ እግዚእ ኢየሱስ ዘእንበለ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌሁ› እንዲል መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያላደረበት ማንም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጣሪ ነው ብሎ መናገር የሚቻለው  የለምና ወደ አሚነ ሥላሴ የሚመራ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የምናገኝበት ሥርዓተ ጥምቀትን አስቀድሞ ተናገረ፡፡ ነገር ግን ኒቆዲሞስ ልደቱ ሥጋዊ ልደት መስሎት ነገሩ ቢረቅበት ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብሎ ክርክር ገጠመ ጌታም አስረደቶት ሊገነዘብ ባለመናቻሉ፣ ባለማወቁ ሳይሆን ክርክር በማብዛቱ “ወይቤሎ አንተ ሊቆሙ ለእስራኤል ወዘንተ ነገረ ኢተአምር” ‹‹አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን እንዴት አታውቅም?›› በማለት አለምልሞ  ገሠፀው!
‹አንተ መምህር ስትሆን ይህን እንዴት አታውቅም?›
          የቤቴን ሥርዓት በሚገባ በጠበቁ፣ አገልግሎታቸውንም በሕይወታቸው በፈጸሙ፣ ቃሌን ያለመቀላቀል ያለ ግላዊ ሐሳብና ብሶት ለሕዝቡ በሚገባ ባደረሱ ንጹሕ ቧንቧዎቼ በሆኑ እርስ በእርስ ተፋቅረው የፍቅር አምላክነቴን በገለጡ እምነትን ከሥራ፣ ሰብከትን ከአርአያነት ጋር አስተባብረው በያዙ በባሪያዎቼ በሐዋርያት እግር ለተተካህ እንደ ጳውሎስ ሰባኪ፣ እንደ ሉቃስ ጸሐፊ ለሆንክ ለአንተ የልብህ በር የተግሳጼን ቁርቁር (ኳኳታ) ቢሰማ ቃሌንም ቢያደምጥ ሥራህን ከሥራቸው፤ እምነትህን ከእምነታቸው መዝኜ ቀለህ ስለተገኘህ አባት የሚወደውን ልጅ ከቅጣት በፊት እንዲገስጽ እንዲሁ እገስጽህ ዘንድ እነሆ የተግሳጼ ቃል!  
በቤቴ አምስት እና ስድስት ዓመታት ስታስቆጥር፣ ቃሌን ስትማር ምስጋናዬን ስትደግም፣ ለአገልግሎት ደፋ ቀና ስትል ብዙዎችን ስትመክር፣ ከስህተት መንገድ ስትመልስ ለብዙዎችም ብርሃን ስትሆን እራስህን ግን መጐሠምና ነፍስህን አንዳትጣል ማረምን፣ እራስንም ማገለግል እንዲገባ ‹አንተ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?›
          ለሌሎች መስገድና መጾምን መጸለይን ስታስተምር፣ ከማይገቡ ከእኩያት ተግባራት እንዲርቁ ስትመክር፣ መልካም ምግባር እንዲኖራቸው ስትዘክር፤ እነዚህ ሁሉ የምክር ቃላት፣ የጽድቅ መንገዶች ለአንተ ብትጠብቃቸው በቃልህ /ባልከው/ ብትመራባቸው፣ በመንገዱ ብትሄድበት የሚጠቅምህ መሆኑን ‹አንተ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?›
          የግብፅ አስረኛ መቅሠፍት በኩረ ሞትን ስትሰብክ፣ የበግ ደም ከተቀቡ ቤት ፊት ለፊት ያሉ ቤቶች በመልአከ ጽልመት መጐብኘታቸውን ስታስተምር፣ አንተ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ቆመህ ስትሰብክ፣ ከአበው ምንጭ የሆነውን ወንጌል ስትናገር፣ ምስጢርን ስትመሰጥር በአንደበት ለዛህ በቃላት አጣጣልህ ተማርኮ ሰው ሲያደንቅህ፣ ይባስ ብሎ የወንጌሉን ጌታ ረስቶ ሲከተልህ ውዳሴ ከንቱ ሽተህ ነገሩን በእጄ ብለህ መቀበልህ፣ ነገረ መስቀሉን ከሕዝቡ ሕሊና ማራቅህ እንደ ግብጻውያን ፍዳ መቅሠፍተ ኩነኔ እንደሚያመጣብህ ‹አንተ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅም?›
          የፈሪሳውያንን ታሪክ አያነበብክ፣ ወግ አጥባቂነታቸውን ቀንበር ጫኝነታቸውን እያወቅክ፣ በሠርኩ ጉባኤ ነጭ ሠናፊል /ልብሰ ወንጌል/ ለብሰህ ሕዝቡን ምግባር ትሩፋት እንዲያደርጉ  ስትመክር ስትዘክር ቆይተህ ገና ከአውዱ /ከአውደ ምሕረት/ ሳትወርድ ለሕዝቡ መሰናከያ ማስቀመጥህ፣ ካህናት አባቶችን መዝለፍህ፣ ርዕሰ መምህራን የሆንኩ የእኔን ‹አሠረ ፍኖት ይዘሃልና› ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ… እንዲሉ  አበው ባንተ ምግባረ ጎዶሎነት እና ንዝህላልነት ነቀፌታ የሌለብኝ እኔ እንደምነቀፍ በአሕዛብ ዘንድ እንደምሰደብ እንደምዘለፍ ‹አንተ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?›
ቆዲሞስ በአገልጋዮች እይታ
ቆዲሞስ በሌሊት ይመጣ የነበረው ምንም ብዙ ምክንያት ኖሮት ቢሆንም በክት ልቦና ብናስተውለው በአገልጋይ ዓይን ብንመለከተው ግን አንድ ለኛ መካሪና ገሣፂ የሆነ ምግባር ሆኖ አናገኘዋለን፡፡  ይኸውም ኒቆዲሞስ ለቃለ ወንጌል ካለው ጥማትና ፍቅር የተነሳ በሌሊት ‹ብድርን የሚያህል ስቃይ እንቅልፍን የሚያህል ሲሳይ› ትቶ ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ይማር ነበር፡፡ በእውነት ይህ ትጋቱ ለእኛ ብዙ ነገር ያስተምረናል፡፡ ጠዋት ቤተክርስቲያን ፍሪዳዋን አርዳ ምሦሶዋን ተክላ ኑ ልጆቼ! በእለተ ሰንበት ከማዕዴ ተካፈሉ፡፡ እርሱስ ባይሆንላችሁ አስቀድሱ ብላ ስታውጅ እኛ ግን ጥሪዋን ንቀን ፍቅሯን አንቃረን ሥጋው ደሙን በመቀበል ፈንታ ኃጢአትን እንደ ውሃ እያጣጣምን ስንጠጣ እንደ ምግብ ስንመገብ እንኳን ከነዊመ ሥጋ (ከሥጋ እንቅልፍ) ቀርቶ ከነዊመ ነፍስ (ከነፍስ እንቅልፍ) የሚቀሠቅስ ድምጿን ላቃለልነው ለእኛ የኒቆዲሞስ ሕይወት መጽሔት /መስታወት/ ሆኖ ብንመለከትበት መንፈሳዊ አቋማችንን ከመታዘባችን ሌላ ለመፈረጃም እንደሚሆን ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል፡፡ ሌሊት የተባለ መከራ ብርድ ስቃይ አንቅልፍ ማጣትን ተቋቁሞ ተግቶ ቃሉን መስማት እንዲሁም ማገልገል ህልፈት ጥፋት የሌለው የዘላለም እረፍት ያለበትን እርስት ነውና የሚያቀዳጀን ተግተን ወንጌልን ልንማር ይገባል!
‹‹የአምላክን ከሃሊነት መስክሯል!!!››
          ኒቆዲሞስ የአምላኩን የመምህሩን ከሃሊነት በማያሻማ ግልጥ በሆነ ቃል መስክሯል፡፡ በዚህም የተነሣ ጌታ ይህን እምነቱን እና ጽናቱን /ልፋቱን/ አይቶ አስቀድሞ እንዲሁ ለመማር እንደመጣ በኋላም ቅዱስ ሥጋውን መጥቶ ይገንዝ ዘንድ ከበረከቱ ተካፋይ እንዲሆን መርጦታል አክብሮታል፡፡ እንዲሁ እኛም የምንማረው ቃል እግዚአብሔር የምናየውን ገቢረ ተአምር ለዓለም ልንመሠክር ግድ አለብን፡፡ ታዲያ ይህንን ተልዕኮአችንን በመዘንጋት አምላካችን እግዚአብሔር ያለው በቤተ ክርስቲያን ቃሉም የሚሠበከው በአውደ ምሕረቱ  ብቻ እየመሠለን  ከቤተ ክርስቲያን በአፍአ ወይም በውጪ ለሚነሡ ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ስንል በምን አገባኝ ባይነት መንፈስ ስናልፍ ይስተዋላል፡፡ ይሁንና ግን ሰው ክፉ ነገር ከመናገር ክፉ ነገር ከማሠብ ሊጠበቅ ይገባዋል እንጂ የነገረ ሃይማኖት ሐሳቦች ሲነሡ  የምንፍቅና ጥያቄዎች ሲሠነዘሩ ዝም ብሎ መመልከት የለበትም፡፡ ደግሞም የራሱ ክብር ሲነካ ‹የነብር አራስ› የሚሆነው ስመ እግዚአብሔር ሲዘለፍ ምስጢረ ሃይማኖት ሲነቀፍ ደርሶ ትዕግስተኛ ልሁን ማለት ከአምላክ ጋር ሳያስተዛዝበን አይቀርም! ‹ስለ ጽዮን ዝም አልልም› ተብሎ የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መልእክትነቱ ለሁላችንም ነውና ስለ ጽዮን መናፍቃንን ልንረታ ስለ ጽዮን ድምፀ ቤተክርስቲያን ልናሠማ ይገባል፡፡
‹‹መምህር ሆኖ ይማር ነበር!!!››
          ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት መምህረ አይሁድ ሆኖ ሳለ ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ተምሯል፡፡ ምንም ውዳሴ ከንቱ ሽቶ ማታ እየመጣ ይማር የነበረ ቢሆንም መምህር ሆኖ መማሩ በራሱ እንደ ጊዜው ሁኔታ ሊያስመሰግነው የሚገባ ምግባር ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌሎች ምሁረ ኦሪት ኦሪትን አወቅን እንደሚሉት እንደ ፈሪሳዊያን እውቀት ተከቶልኛል፣ ምስጢር ተደላድሎልኛል ብሎ አራሱን ከትምህርት ገትቶ አልተቀመጠምና፡፡ ወደ እኛ  ሕይወት ስንመለስ በጉባኤ ቁጭ ብለን የተማርናት ጥቂት ቃለ እግዚአብሔር፣  ያነበብናቸው ሁለትና ሦስት መጻሕፍት እንዳንማር ቃለ እግዚአብሔርን አንዳንሰማ አንቃ ትይዘናለች፡፡ ከዚህም በላይ ብዛቱና  ጥልቀቱ የማይመረመር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አውቀናል ወደሚል ታላቅ የትዕቢት አዘቅት ሲጥለን ይታያል፡፡ በተጨማሪም ስንበድል  ስናጠፋ በጓደኞቻችን እንዲሁም በመምህራነ ቤተክርስቲያን እንዳንመከር ጥቂት እውቀታችን ከሰው ሁሉ በላይ አድርጋ ለኛ መማር እና መመከር እንደማይገባን፣ ስህተቱንም ቢሆን ሌላ አመክንዮ /ምክንያት/ አቅርበን ተሸፋፍነን እንድናልፍ በማድረግ በኋላም ‹እስመ ርዕሳ ለክሕደት ጸጊበ ትምህርት ውእቱ› ‹የክህደት ራሷ ትምህርትን መጥገብ ነው› እንዲል እስከ ሃይማኖት ክህደት የሚያደርስ ብዙ ጣጣ ይዛብን ትመጣለች፡፡ መድኃኒታችንም ቢሆን የእውቀት ተከፍሎ የሌለበትና እውቀት ለሌላቸው እውቀትን በልግስና የሚሰጥ አምላክ ከመምህራን እግር ስር ቁጭ ብሎ መማሩንና መጠየቁን እያነበብን  ‹የእርሱን  የእሩብ እሩብ ኢምንት› የማትሆን ጥቂት እውቀት ይዘን ለመማር ለማንፈቅድና ለማስተማር ለምንፈጥን ወዮ የፍርድ ቀን ወዮ!
‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር መጽንኤ ለድኩማን አግብርቲሁ››
‹‹ደካማ ባሪያዎቹን ለሚያፀና እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን››
ዲ/ን አቤል ካሣሁን

No comments:

Post a Comment