በስመአብ ወወልድ ወመንፈቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ዐቢይ ፆም
ማቴ. 4፡1-11 ፤ ማር.1፡12-13 ፤ ሉቃ. 4፡1-3
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየአመቱ መጥቅዕና አበቅቴ ሰፍራ ቀን ከምትወስንላቸው በዓላትና አጽዋማት መካከል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረተልን ዐቢይ ፆም አንዱ ነው፡፡ በዓሉም ዐቢይ (ታላቅ) መባሉም ቅሉ ዐቢይ (ታላቅ) የተባለው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመው ነው፡፡ መጾሙም ጾም የሚያሻው ሆኖ ሳይሆን ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ጾመ እግዚእነ በእንቲአነ አርአያሁ ከመ የሃበነ- ጌታችን ስለኛ ጾመ አብነቱን (ምሳሌውን) ይሰጠን ዘንድ” እንዳለ፡፡ ይህ ታላቅ ጾም ዐቢይ ከሚለው ስያሜ በተጨማሪ አዳም በመብል ምክንያት ያጣውን ልጅነት ሊመልስለት የጾመው በመሆኑ የካሳ፤የትምህርት አገልግሎቱን ከመጀመሩ አስቀድሞ የጾመው በመሆኑ የዝግጅት ፆም፣ጠላት ዲያቢሎስን ያሳፈረበት በመሆኑ የድል ፆም እንዲሁም ሁዳድ ተብሎ እንደሚጠራው ሰፊ እርሻ መሬት የፆሙ ቀናት ሰፊ በመሆናቸው የሁዳድ(ዴ) ፆም እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚህም ሌላ ፆመ አርብዓ የሚል ስያሜ ሲኖረው በወንጌላት እንደተገለፀው ጌታችን ቀደምት ነቢያት አበው (እነ ሙሴ፣ ኤልያስ) በፆሙት አምሳል አርባ ቀንና ሌሊት መፆሙን የሚያስታውስ መጠሪያ ነው፡፡ ይህ ስያሜ አሁን ከምንፆመው ፆም ከቅድስት እስከ ሆሳዕና ያሉትን ብቻ የሚያመለክት ሲሆን ከዘወረደ እስከ ቅድስት ያለው አንድ ሣምንት ፆመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሕርቃል የተባለው ክርስቲያን ንጉሥ በአመጻ ተነስቶ ንግስት እሌኒ ካስቀመጠችበት መቅደስ መስቀሉን የዘረፈውን ዓላዊ ንጉሥ ተዋግቶ መስቀሉን ማስመለሱን በማሰብ እንዲጾም፤ እንዲሁም ከሆሳዕና እስከ ትንሳኤ ያለውን አንድ ሣምንት ደግሞ ሰሙነ ሕማማት ተብሎ የጌታ መከራና ስቃይ እንዲታሰብበትና እንዲጾም ቅዱሳን አባቶችን በሠሩት ሥርዓት የተጨመሩ ናቸው፡፡
ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም በሦስት ወንጌላት (በማቴዎስ በማርቆስና ሉቃስ) የተዘገበ ሲሆን በማቴዎስና ሉቃስ ጌታችን የተፈተነባቸው ሶስት ፈተናዎችም በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
እነዚህ ሦስት ፈተናዎች አርእሥተ ኃጣውእ (የኃጢአት ራሶች) ሲባሉ የሌሎች ኃጢአቶች ምስጢራቸውና መነሻቸው እነዚህ ሦስት ኃጢአተኞች ናቸው፡፡ እነዚህም ሆድን መውደድ(ስስት) ተርእዮንና ክብርን መሻት (ትዕቢት) ገንዘብን ያለልክ መውደድ (ፍቅረ ንዋይ) ናቸው፡፡ ጌታችን ስስትን በትዕግሥት፣ ትዕቢትን በትሕትና፣ ፍቅረ ንዋይን በፀሊዓ ንዋይ (ገንዘብን በመናቅና በመጥላት) ድል አድርጎ ድል እናደርግ ዘንድ ምሣሌ ትቶልናል፡፡
የዲያቢሎስ ፈተናዎች አቀራረባቸውና ሥልታቸው ምን ዓይነት እንደሆነም ከወንጌላቱ እንማራለን፡፡ በመጀመሪያው ፈተና ይህን ድንጋይ ዳቦ አድርግና እንብላ ብሎ ራሱን የማይችል አድርጎ ዝቅ አድርጎ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ በሁለተኛው በተገዳዳሪነት (በእኩያነት) መንፈስ እስቲ ራስህን ጣልና ያድንህ ይሆን አያድንህ እናያለን ብሎ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡ በሦስተኛው ደግሞ ወድቀህ ከሰገድክልኝ ይህን እሰጥሃለው ብሎ የበላይነትን ተላብሶ አድራጊ ፈፃሚ ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ይህም ዲያብሎስ ያነሰም እኩያም የበለጠም መስሎ እንደሚፈትነን የፈተናው አመጣጥም ከትንሽ ወደ ትልቅ እያደገ እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ጌታችን “እንዲህ ተብሎ ተፅፏል” እያለ መመለሱ ደግሞ የዲያብሎስን ፈተናዎች ለማሸነፍ ቃለ እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ እንዳለብን ያስተምራል፡፡ ሐዋርያው “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ……የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” እንዳለ፡፡ ኤፌ 6÷13-17
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የተፈተነ ሆኖ ሳለ በተለየ መልኩ በእነዚህ ወንጌላት ይፈተን ዘንድ የሚለው ቃል መገለጹ ዲያብሎስ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ፈተናውን በፆም ወራት እንደሚያበረታ ለማስተማር ሲሆን እኛም የማሸነፉን ብርታት የምናገኘው በዚህ ወቅት ነው በሌላ ቦታ ጌታ “ዝንቱ ዘመድ ኢይወፅእ ዘእንበለ በፆም ወበፀሎት . . . ይህስ ወገን ያለ ፆምና ፀሎት አይወጣም” ብሎ አጋንንትን ያለ ፆም ማሸነፍ እንደማይቻል ያስተማረውን ትምህርት መጥቀስ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ማቴ 21
ፈተናው ከጥምቀቱ በኋላ መሆኑም ለምእመናን የሚሰጠን ትምህርት አለ፡፡ ይኸውም ከማየ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት የተወለዱ ምእመናን ምንም ፈተና ቢበዛባቸው በፆም በፀሎት ከፀኑ ድል የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው፡፡ ቆሮንጦስ ገዳም ለገዳማውያን አባቶች አብነት በመሆንም ይጠቀሳል፡፡ በማርቆስ ወንጌል እንደተፃፈው ጌታ አናብስት (አራዊት) ወደ ነበሩበት መሄዱ ድምፀ አራዊቱን ግርማ አራዊቱን ታግሰው ፀብዓ አጋንንትን (የአጋንንትን ፈተናና ጥል) ድል ያደረጉ ፃድቃን አበውና እማትን ያዘክረናል፡፡ እነዚህም ፃድቃን እንደ ጌታችን ሁሉ መላእክት ተገልጠው እንዳገለገሏቸው በገድላትና በተአምራት መጻሕፍቶቻቸው የተዳሰሱት ታሪኮቻቸው ይናገራሉ፡፡
ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ በፈተናዎቹ ውስጥ መጻሕፍትን አዋቂ መስሎ ቀርቧል፡፡ ይኸውም በመጀመሪያውና በሁለተኛው ፈተና በግልፅ የሚታይ ሲሆን በመጀመሪያው መልአከ እግዚአብሔር ለወንድሞቹ ስንቅ ያደርስ ዘንድ ተልኮ ሳለ ረሃብ ቢፀናበትም የእነርሱን ላለመብላት ለጨከነ ዮሴፍ ድንጋዩን ዳቦ እንዳደረክለት በማለት በትውፊት የተነገረውን ይዞ ሲጠቅስ፣ በሁለተኛው ደግሞ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት መዝሙር አንዲት ሐረግን መዝዞ ጠቅሷል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ንግግሮቹ ውስጥ የሐሰት ትምህርቶች ተካተውበታል፡፡ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ በል” በሚለው ውስጥ የእግዚአብሔር ልጅ ካልሆንክ ተአምራት መፈፀም አትችልም የሚል ሐሳብ ሲንፀባረቅበት ይህም የእግዚአብሔር ልጅነት መለኪያው ተአምራትን መፈፀም መቻል መሆኑን ይሰብካል፡፡ የመጀመሪያው የሐሰት ትምህርት ይህ ነው፡፡ ተአምራትን የፈፀሙ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉምና፡፡ “መላእክቱን ስላንተ ዲያብሎስ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተፅፏል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ ወደታች እራስህን ወርውር” በሚለው ሁለተኛ ፈተናው የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫቸው ከመከራ መትረፍ እንደሆነ ያስተምራል:: በዚህ ቦታ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በሌሎች አስገዳጅነት መከራ ሲመጣ በእግዚአብሔር ሊፈጸም የሚችለውን የማዳን ሥራ ተናገረ እንጂ በራሳቸው ተነሳስተው መከራ ውስጥ ለሚገቡት አልተናገረውም፡፡ በዚያውም ላይ ይህ የሚፈፀመው ለተወሰኑቱ እንጂ ለሁሉ አይደለም፡፡ ቅዱሳንም ይህን አውቀው ለመከራ በተዘጋጁ ጊዜ እንደ ሠለስቱ ደቂቅ “እግዚአብሔር … ያድነን ዘንድ ይችላል ባያድነንም እንኳ” ብለው ይናገራሉ፡፡ ዳን 3÷16
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ስለእምነት አርበኞቻችን ሲጠቅስ ከቆየ በኋላ በማጠቃለያ መልእክቱ ተአምራት ተደርጎላቸው ከመከራ ስላመለጡ ቅዱሳን “እነሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ… የአንበሶችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትንም ኃይል አጠፉ…” ሲል የእግዚአብሔርም ጥበብ በመዳናቸው ሳይሆን በሞታቸው ስለተገለጠባቸው ቅዱሳን ደግሞ “ተወግረው ሞቱ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ…” በማለት ተናግሯል፡፡ ዕብ 11÷33-37
ይህም የሚያሳየው የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫቸው ከመከራ መትረፍ ብቻ ሳይሆን በመከራ ማለፍም ጭምር መሆኑን ነው፡፡ ያውም ቢሆን መከራው የሚመጣው ከሌላ ወገን እንጂ ከራሳቸው ፈቃድ (ተነሳሽነት) አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብ እራስን ወደ መከራ በመክተት ሳይሆን ሌሎችን ከመከራ በማውጣት ይገለጣልና፡፡ በመጨረሻው ፈተና ደግሞ ዲያብሎስ የዓለምንም መንግስታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ብሎ መፈተኑ ተፅፎአል፡፡ በዚህ ቦታ ዲያብሎስ ሰጪ መስሎ የቀረበ ሲሆን ከመስጠቱ አስቀድሞ እንዲሟላለት የጠየቀው ተገዢነትን ነው፡፡ ወድቀህ ብትሰግድልገኝ የሚለው ቃል ትርጉሙ ይህ ነውና፡፡ እኛን ገዝቶ ምንም ቢሰጠን ሰጠ ይባላልን? ወድቀን ብንሰግድለት እንኳን እሰጣችኋለው ያለውን የሚሰጥ አይደለም፡፡
ይህም ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራችሁን አቀልላችኋለሁ ብሎ ለአዳምና ሔዋን ከመከረ በኋላ ጽፈው ቢሠጡት በፈቃዳቸው ለመገዛታቸው እንደ ማስረጃ ይዞ መከራ ማፅናቱን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ምንም ብናደርግለት ይሄን አድርገውልኛልና እንዲህ ላድርገላቸው የሚል ደግ አስተሳሰብ ከዲያብሎስ መጠበቅ ከዝንብ ማር ከበሬ ወተት እንደመጠበቅ ያለ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ዘመጽአ ወአደኀነነ እምእደ ፀላዒ ዘአልቦ ምሕረት- መጥቶ ምሕረት ከሌለው ጠላት እጅ ያዳነን” በማለት ዲያብሎስን ምሕረት አልባ ማድረጉ ለዚሁ ነው፡፡ ከነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ዲያብሎስ እውነት ተናጋሪ ይምሰል እንጂ በምንም ዓይነት ሁኔታ እውነት የማይናገር ሐሰተኛ የሐሰትም አባት መሆኑን እንማራለን፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለውን አጭበርባሪ በየጠበል ቦታው ትምህርት ይሰጥ ዘንድ መጋበዝና በካሴት ቀርጾ ለሕዝብ ማዳረስ አደጋ አይመስላችሁምን? ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም ይህን አይፈቅድም፡፡
የጌታችን ፆምና ፈተናዎቹን ከዚህም ዉጪ የሚያስተምሩን እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ ፡፡ እነዚህን ደግሞ ለአንባቢያንና ለሌሎች ጸሐፊያን ትተን የእኛን በዚህ እናብቃ ፡፡
ፆሙን የበረከት፣ የፍቅር ፣የሰላም ፣የንሰሃ ፣ያድርግልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዲ. ተስፋሚካል አሰፋ
No comments:
Post a Comment