· በተዘክሮ
ተዘክሮም እንዲሁ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብክበት አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ይህም አንድ ክርስቲያን በሚፈጽማቸው መንፈሳዊ ተግባራት ነገረ ክርስቶስን እንዲያስብ ያስችለዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሚያማትብበት ወቅት በቅድምና የነበረ አካላዊ ቃል ወልድ የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማያዊ መንበሩ መውረዱን፣ በተለየ አካሉ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን(ሥጋ መልበሱን)፣ በዕለተ አርብ ተሰቅሎ ሞቶ ሥጋው በመቃብር ሲያድር በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በዚያ ያሉ ነፍሳትን ወደ ገነት መመለሱን፣ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቶ ወደ ሰማይ ማረጉን ያስባል፡፡ እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ጌታ በሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር የፈጸመውን የማዳን ሥራ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአንድ እጅ ጣቶችን በማመሳቀል በሚፈጸም እንቅስቃሴ /ማማተብ/ ማሰብ መቻሉ ነው፡፡
በቅጽረ ቤተክርስቲያን የተገኘም አንድ ሰው የሕንጻ ቤተክርስቲያኑን መዋቅር፣ ጉልላት መስቀሉን ሲያይ ልብ ያለ እንደሆነ ጌታ በዕለተ አርብ በቀራንዮ ተራራ መሰቀሉን፣ ክርስቶስም የቤተክርስቲያን ራስ መሆኑን እንዱያስብ ግድ ይለዋል፡፡
እነዚህ የጠቀስናቸውና ያልዘረዘርናቸው ሌሎችም አንድ ክርስቲያን ዘወትር በማናቸውም ቦታ ቢሆን አምላኩን እንዲያስብና እንዲህ የሚለውንም የእግዚአብሔርን ቃል እንዲፈጽም ያግዙታል፡፡ “እኔም ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሳም ተጫወተው፡፡ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ፡፡” ዘዳ. ፮፥፬ ነገር ግን የሚያየውንና የሚሰማውን የሚያስተውል ጥቂት ነውና ብዙዎች ይስታሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ መኑ አሕመመክሙ ከመ ኢትእመኑ በጽድቅ ከመ ያስተርኢ ለዓይን ኢየሱስ ክርስቶስ” “እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ ለጽድቅ እንዳትታዘዙ ማን አታለላችሁ? ቀድሞስ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓይናችሁ ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር” ያለው ከቶ ለማን ሆነና? ነገረ ክርስቶስ በዓይናቸው ፊት ተስሎላቸው ሳለ ላላስተዋሉት አይደለምን?
በተጨማሪም በዝማሬ ወቅት ማሸብሸብ ማጨብጨባችን፣ በማኀሌቱ ሥርዓትም የሚታዩት የከበሮ፣ የመቋሚያና የጸናጽል እንቅስቃሴዎች ሁሉ ነገረ ክርስቶስን ሰባኪዎች ናቸው፡፡ ስለ እያንዳንዳቸው እንዳንዘረዝር በየራሳቸው ሰፊ ትንታኔ አላቸውና ይህን ለማድረግ ጊዜና ቦታ ይገድበናል፡፡
· ስሙን በመጥራት
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃያልና ከስም ሁለ በላይ የሆነ ስሙን በመጥራት እርሱን መስከብ ሌላው መንገድ ነው፡፡ ይህም ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን ዕሪና (ትክክልነት) ሳያጓድል የሚፈጸም ነው፡፡ ስለዚህም በእንተ ማርያም እሙ፣ በአማኑኤል ስሙ ብሎ ይማረን፡ በማለት በጸሎት ወቅት ስሙን በመጥራት፣ “ንሰግድ ለከ ክርስቶስ ምስለ አቡከ ኄር ሰማያዊ ወመንፈስከ ቅዱስ ማሕየዊ” “ክርስቶስ ለአንተ እንሰግድልሃለን ከሰማያዊ ከቸር አባትህ ጋር አዳኝ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር” በማለት ለአምላክነቱ የሚገባውን ስግደት በማቅረብ ስሙን እየጠራች ታከብረዋለች፡፡ “ዝ ውእቱ ጊዜ ባርኮት፤ ወዝ ውእቱ ጊዜ ዕጣን ኅሩይ፡፡ ጊዜ ሰብሖቱ ለመድኃኒነ መፍቀሬ ሰብ ክርስቶስ” “የማመስገን ጊዜ ይህ ነው፤ የተመረጠ የዕጣን ጊዜም ይህ ነው፡፡ ሰውን ወዳጅ የሆነ መድኃኒታችን ክርስቶስን ማመስገኛም ጊዜ” በማለት ደግሞ የሚገባውን ውዳሴ ለምስጋና የሚሆን ጊዜ ሰጥታ ታቀርባች፡፡
ቤተክርስቲያን ክርስቶስን እንደ ክርስቶስነቱ የማትጠራበት ጊዜ የለም፡፡ የስሙም ጣዕም ዘወትር ከአንደበቷ የማይጠፋ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ስም ለዘይጼውዖ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ቃል ለዘያጸምዖ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ሥጋ ለዘይበልዖ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ደም ለዘይሰትዮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ፄና ለዘያፄንዎ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ዝክር ለዘይነግር ዜናሁ ” “ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያዳምጠው ቃሉ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው ሥጋው የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው ደሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዜናውን ለሚነግር መታሰቢያው የጣፈጠ ነው ” ያለው መቼ በከንቱ ሆነና (መጽሐፈ ምሥጢር፣ የዕርገት ምንባብ):: ስለሆነም ቤተክርስቲያን ስመ ክርስቶስን ከመጥራት የምትከለከልበት ጊዜ የለም አይኖርምም::
ከዚህ ባሻገር በማናቸውም ሥራ “በስመ አብ ወወልዴ ወመንፈስ ቅደስ አሐዱ አምላክ በማለት ስሙን በመጥራት ጀምራ፣ ስብሐት ለአብ ወወልዴ ወመንፈስ ቅዱስ በማለት ስሙን እየጠራችና እያመሰገነች ተግባሯን ትፈጽማለች፡፡
· በአዋጅ
ሌላኛው የስብከት መንገድ በአዋጅ የሚደረግ ነው፡፡ ይህም ቃለ አዋዲ /የአዋጅ ነጋሪ ቃል/ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ያደርግ እንደነበረ ሁሉም ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንገድ የተባለ ልቡናውን በእምነትና በምግባር ጎዶሎውን እየሞላ፣ ጠማማውን እያቀና ራሱን ለእግዚአብሔር መንግስት እንዲያዘጋጅ የምታውጅበት ነው፡፡ ዲያቆኑ በቅዳሴ “ሃሌ ሉያ ቁሙ ወአጽምዑ ወንጌለ ቅዱሰ ዜናሁ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ” “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቅዱስ ወንጌል ቁማችሁ አድምጡ” በማለት ያውጃል፡፡ ይህን አዋጅ የሰማ ሁሉ ቃለ ወንጌሉን ይሰማ ዘንዴድ ይዘጋጃል:: ቤተክርስቲያን ወንጌሉን በአዋጅ ስትሰብክ ሰሚው ደግሞ ዝግጁ ሆኖ፣ ሐሳበ ልቦናውን በመሰብሰብ የክርስቶስን ትምህርት ለመስማት የተዘጋጀ እንዲሆን ታደርጋለች፡፡ በተጨማሪም “----ረስየነ ድልዋነ ንስማዕ ወንግበር ቃለ ወንጌልከ ቅዱስ በጸሎቶሙ ለቅዱሳን” ብዙዎች ሊሰሙ እና ሊያዩ ሲወዱ ያላዩትንና ያልሰሙትን ቅዱሱን ቃልህን ለመስማት ሰምተንም ለመተግበር አብቃን፣ ለዚያ የሚያበቃ ምግባር ሃይማኖት ባይኖረንም በቅዱሳን ጸሎት የወንጌልህን ቃል ለመስማት መጨከንን፣ ሰምተንም መተግበርን ስጠን በሚል ጸሎት ታሳስባለች፡፡ በአዋጁም ቃሉ የሚዘራበት ልቡና እንዲለሰልስ መልካም ፍሬ /የመንፈስ ፍሬ/ እንዲያፈራ ቀድማ ታዘጋጃለች፤ ልጆቿ ቃለ ወንጌሉን ይሰሙ ዘንድ ስታዘጋጅ በጎኑ ደግሞ በሰሙት ቃል ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ወደ አምላኳ ትማልዳለች፡፡ ይህ በቅዳሴው ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያን በምትፈጽማቸው ሌሎች ምሥጢራትም ይከናወናል፡፡ ቃሉን ሰምተው በተግባር የሚፈጽሙት ደግሞ በመልካሙ ሥራቸው ለጨለማው ዓለም እያበሩ አምላካቸውን ያስመሰግናሉ፡፡ ሌሎችንም ወደ እርሱ ያቀርባሉ፡፡
በዚህ ጽሑፍ በጠባብ አዕምሮ በደረቅ ብዕር ቤተክርስቲያን እንዴት ክርስቶስን እንደምትሰብክ እጅግ በጠባቡ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ይህ ማለት ግን ክርስቶስ በቤተከርስቲያን በእንዲህ መልኩ ብቻ ይገለጣል ማለት አለመሆኑ ከጉባኤዋ ለዋለ፣ ጣዕመ ትምህርቷን ለቀመሰ፣ በቤተመቅደሷ ለኖረ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡
ቤተክርስቲያን ያልሰበከችው ክርስቶስ አለ ከተባለ ሐሰተኛው ክርስቶስ ነው፡፡ እሱ ደግሞ ወደፊትም የማትሰብከው ነው፡፡
እንዲህ ከሆነ ታዲያ እንዴት ክርስቶስ በቤተክርስቲያን አልተሰበከም ይባላል? ይህ ሰሚውን የሚያደናግር ቃልስ ከወዴት ተገኘ? ምንጩስ ከየት ነው? እንጃ ያሰጋል፡፡ ሐዋርያዊት የሆነች ቤተክርስቲያን ከንጹሐን የሕግ ምንጮች ከሐዋርያት የተገኘውን ጥሩ(የጠራ፣ ያሌደፈረሰ) ትምህርት ይዛለች :: እርግጥ ነው ኮለል ወዳለ ምንጭ የወረደ ሁሉ ንጹሕ ውኃ ላይቀዳ ይችላል:: እንደ አቀዳዱ አደፍርሶ የሚቀዳም አለና እንዲህ ካለው መጠበቅ ይገባል፡፡
ከዚህ ሁሉ ጋር ቤተክርስቲያን ስንል በዘይቤአዊ ፍቺው እያንዳንዱን ምዕመንም(ክርስቲያን) በተናጥል ይመለከታልና በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በውስጣችን ያለውን ክርስቶስን በመምሰል፣ በመልካም ሥራችን ብርሃንነት ያላወቁት እንዲያውቁት በእኛ ሕይወት ይገለጽ ዘንድ ይገባል፡፡
በተቀረውስ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በቃሉ ጸንተን፣ እርሱን መስለን፣ እርሱን ገልጠን መኖርን ያዴለን፡፡ የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎትና ምልጃ አይለየን፡፡
“እመሂ ስሕትኩ አንትሙ እለ በመንፈስ አርትዕዎ”
“የተሳሳትኩትም ቢኖር እናንተ በመንፈስ ያላችሁ አቃኑት”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ማስረሻዬ ወርቁ
No comments:
Post a Comment