ውዳሴ ከንቱ
ውዳሴ ከንቱ የሚለው ቃል የማይረባ የማይጠቅም ውዳሴ የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን ውዳሴ ብጡል (የተናቀ፤ ተርታ) ውዳሴ ተብሎም ይጠራል፡፡ የቃሉ ትርጉም በዚህ መልኩ የሚፈታ ይሁን እንጂ “ የማይጠቅም “ ከመሆን አልፎ ሰውን ሊጎዳ የሚችል ነገር በመሆኑ የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት አጥብቀን ልንሸሸው እንዲሚገባ ያስተምራሉ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩ ስር ተቀምጣ ቃላት ታዳምጥ የነበረችውን የማርታ እህት ማርያምን “ማርያምስ የማይቀሟትን በጎ ዕድል መረጠች ” ሉቃ10÷42 ብሎ ያመሰገነበትን ቃል አበው ሲተረጉሙ “ መማር ውዳሴ ከንቱ የለውም “ አላውቅም ማለት ነውና፡፡ ስለዚህም አጋንንት የማይቀሟትን (ዋጋዋን ) የማያስቀሩባትን መማርን መረጠች ማለት ነው ብለው መተርጎማቸው ‹‹ውዳሴ ከንቱ›› የሰውን የልፋት ዋጋ በምድራዊ ክብር የሚያስቀር ከንቱ ነገር መሆኑን ያስረዳል፡፡ አበው ከውዳሴ ከንቱ እንድንጠበቅ ማስተማራቸው የመልካም ስራችን ዋጋ ሰዎች በሚያቀርቡልን የምስጋና ስጦታ ምክንያት በምድር እንዳይቀርብን በማሰብ ነው፡፡ በወንጌልም ጌታ ከሰዎች ምስጋና በመሻት መልካም ሥራቸውን በሰው ፊት ስላደረጉ ፈሪሳውያን ሲናገር “እሙንቱሰ ነሥኡ እሴቶሙ… እነዚህስ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” ማቴ6÷2 በማለት ከሰው የተቀበሉት ምስጋና ሰማያዊ ዋጋቸውን እንዳሳጣቸው አስተምሯል፡፡
እንዲህ ስንል ግን በሰው የተመሰገነ ሁሉ ውዳሴ ከንቱ ሆኖበታል ያልተመሰገነ ደግሞ አልሆነበትም ማለትም አይደለም፡፡ በልቦናው የመመስገን መሻት ኖሮት መልካም ሥራ የሠራ ነገር ግን በለስ ያልቀናው ያልተመሰገነ ሰው ሊሰርቅ ሄዶ አጥር ፀንቶበት፣ ውሻ ጮሆበት፣ ጠባቂ ነቅቶበት የተመለሰ ሰውን ይመስላል፡፡ መሻቱ በልቦናው ስላለ ሰዎች ባያመሰግኑትም ቅሉ ለመመስገን በመሻት አስቀድሞ ወድቋልና ከሰው ውዳሴ ሳይፈልግ የሠራ ሰውም ሰው ቢያመሰግነው እንኳ አይሻውምና በውዳሴ ከንቱ ወደቀ አያሰኝም፡፡ ይህም ውዳሴ ከንቱ ኃይል አግኝቶ ሰውን የሚጥለው የተዘጋጀ ልቦና ሲኖረው መሆኑን እንገነዘባለን ፡፡
ውዳሴ ከንቱ በሦስት ዓይነት መንገድ ሲቀርብ እንደ አቀራረቡና አቀባበሉም ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡
፩. ሰዎች ስለ እኛ
ውዳሴ ከሰዎች ለእኛ በሚቀርብበት ወቅት የሚያመሰግነን ሰው ማን ነው? ምስጋናውስ ለእኛ የሚገባን ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ከጉዳት ይጠብቀናል ፡፡ የሚያመሰግነን ሰው ማነው? የሚለውን ማሰባችን ተወዳጅነትን ለማትረፍና በአፀፋ ለመመስገን ከሚመጡ ሰዎች ሲጠብቀን ምስጋናው ለእኔ ይገባልን? የሚለውን ማሰብ ደግሞ ምስጋናውን ይገባናል ብሎ ከመቀበል ይጠብቀናል፡፡ በወንጌል ጌታችን “ ቸር መምህር ሆይ “ ብሎ የቀረበው ሰው መመስገንንና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲሉ ምስጋና ከሚያቀርቡ ሰዎች የሚመደብ ነው፡፡(ማር 10÷17) ምስጋናን “ለእኔ የሚገባ ነውን?” ብሎ መርምሮ መቀበልን የተማርነው ከቅዱሳን እናቶቻችንና ከቅዱሳን አባቶቻችን ነው፡፡
ክብር ይግባትና በሚገባት ግብር የተመሰገነች እመቤታችን “እፎኑ ከመ ዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ - እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንዴት ይቀበሉታል?” ሉቃ 1÷29 ማለቷ ቅዱሳን በሚገባቸው ገንዘብ ቢመሰገኑ እንኳ (በትህትና) አይገባንም እንደሚሉ የሚያስረዳ ነው፡፡
በትንሣኤ ዘጉባኤም “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና ….” ተብለው የሚመሰገኑ ቅዱሳን “መቼ ተርበህ አበላንህ?፣ መቼ ተጠምተህ አጠጣንህ?.....” ሲሉ ሠርተው እንዳልሰሩ ሆነው በትህትና እንዲመልሱ ተጽፏል፡፡ ማቴ 25÷44
አቡነ ተክለሃማኖትም ከብዙ ትሩፋትና ተጋድሎ በኋላ “አሌ ሊተ ወይ ሊተ ለዘኢገበርኩ ምንተ - ወዮ ለኔ ምንም ላልሠራሁት” እያሉ ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ገድላቸው ዘግቦታል፡፡
እኛም ምንም እንኳ ከእነርሱ መዐርገ ትህትና ደርሰን አይገባንም ማለት ባንችል በብሩህ ፊት ሆነን ውዳሴን እያጣጣሙ ከመቀበል መለየት ይገባናል፡፡ ይልቁንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት በምንመሰገንበት ወቅት የከፉ ኃጢአቶቻችንን እያሰብን ራሳችን መገሰፅ ይገባናል፡፡
፪. እኛ ስለሰዎች
ምስጋና ከእኛ ስለ ሰዎች በሚቀርብበት ወቅትም ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ሰዎችን ማመስገንና እንዲመሰገኑ መፈለግ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ የበጎ ምግባር መገለጫ ነው፡፡
እንደ ዲያቢሎስ መመስገን ብቻ እንጂ ሰውን ማመስገንና ማበረታታት የማይፈልጉ ሰዎች አሉና፡፡ ነገር ግን የምስጋናውን ልክ የምናልፍ ከሆነ ለተመስጋኙ ጥቅም ከመሆን ይልቅ ፈተና የምንሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡ በውዳሴ ከንቱ የወደቀ ከሆነም መሰናክል የሆንነው እኛ በመሆናችን እንቀጣለን፡፡
“ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ቢኖር የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ከጥልቅ ቢጣል ይሻለው ነበር” ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ማቴ 18÷6 ስለዚህም መመስገን የሚገባውን ሰው መለየትና መመስገን በሚገባው ልክ ማመስገን ከእኛ የሚጠበቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ደግሞም “ከጠላት መሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላል” ተብሎ እንደተፃፈ ለሰዎች ከሚቀርብላቸው ምስጋና ይልቅ ወቀሳና ምክር ለመሻሻል ይጠቅማቸዋልና ማመስገን ብቻ ሣይሆን መውቀስና መምከር ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን የአይሁድ መምህር የሆነ ኒቆዲሞስን “አንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ብሎ አለማወቁን ገስፆ መምህርነቱን አመስግኖ እንደተናገረው የሐ 3÷10
፫. እኛ ስለ እኛ
ውዳሴ ከንቱ ሰዎች እኛን በሚያመሰግኑበት ወቅት ባለን አቀባበል ወይም እኛ ለሰዎች በምናቀርበው ምስጋና ልክ ብቻ የሚመዘን አይደለም፡፡ እኛ ስለራሳችን ባለን አስተያየትና በምናቀርበው ምስጋናም ጭምር እንጂ፡፡በእርግጥ ለራስ ጥሩ አመለካከት መያዝና ራስን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ልክ ከሌለው ግን ለራሳችን ብቻ የምናዜም በውይይት መሃል እኛ ብቻ መነሳት የምንፈልግ ከእኛ ይልቅ ሌላ ሰው ቢነሣ ቅር የሚለን ገፍተንም ስለ ራሳችን ጥሩነት የምናወራ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ “የሌላ ሰው አፍ ያመስግንህ ” ተብሎ መጻፉ ሰው በራሱ አንደበት መመስገን እንደሌለበት የሚያስረዳ ነው፡፡ በወንጌልም የታዘዙትን ሁሉ በፈፀሙ ጊዜ አገልጋዮች ምን ማለት እንዳለባቸው የተቀመጠላቸው ትዕዛዝ “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ” የሚል ነው ሉቃ. 17፡10 ፡፡ ይህም ሰው ከልክ አልፎ ለራሱ ቦታ እንዳይሰጥና በውዳሴ ከንቱ እንዳይወድቅ ለመጠበቅ የታዘዘ ነው ፡፡ እራሳችን ውዳሴ ከንቱ በመሆኑ በማይጠቅም ውዳሴ ላይ ብቻ አተኮረን እንጂ ሚገቡና የሚጠቀሙ የታዘዙም ምስጋናዎች አሉ፡፡ “ የማይጠቅም ውዳሴ ” የሚለውን ርዕስ በራሱ የሚጠቅም ውዳሴ መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድ የሚቀጥለውን ጽሑፍ ስለሚጠቅም ውዳሴ ይዘን እንቀርባለን፡፡
ይቆየን
ዲ/ን ተስፋሚካኤል አሰፋ
No comments:
Post a Comment