Friday, August 5, 2011

ውዳሴ ከንቱ (ክፍል ሁለት)

የሚጠቅም ውዳሴ (ውዳሴ ዘይረብሕ)

ውድ አንባቢያን ባለፈው ጽሑፋችን ስለ ውዳሴ ከንቱ በጥቂቱ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡  በፅሑፉ ፍፃሜ “በሌላ ጊዜ ስለሚገባ ውዳሴ እናቀርባለን” ብለን በገባነው ቃል መሠረት ዛሬ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ጎጂነቱን አውቃ የከለከለችው ከንቱ ምስጋና እንዳለ ሁሉ ተገቢ ነው ይጠቅማል ብላ የፈቀደችው ያዘዘችውም የምስጋና ዓይነት አለ፡፡ ይህ የምስጋና አይነት የተለየ ስያሜ  ባይኖረውም  ከውጤቱ በመነሳት ውዳሴ ዘይረብሕ (የሚረባ-ረብ ያለው ውዳሴ)፣ ውዳሴ ዘይበቊዕ (የሚጠቅም ውዳሴ) ልንለው እንችላለን፡፡

ለአምላካችን እግዚአብሔር፤ለቅዱሳን፤ በሥራቸው ሊመሰገኑ ለሚገባቸው ቅን ሰዎች፤ አንዳንዴም በምስጋና ልናበረታቸው ለሚገቡ ድኩማን የሚደረጉ ምስጋናዎች ከዚህ ዓይነቱ ምስጋና ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡

ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርቡ ምስጋናዎች አመስጋኙን ብቻ ሲጠቅሙ የቀሩት ደግሞ የሚጠቅሙበት ጎዳና ቢለያይም አመስጋኙንም ተመስጋኙንም የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ምስጋና አመስጋኙን ብቻ ሊጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ በቅዳሴ ማርያም ላይ “ዘንተ ቅዳሴ ዘይቄድስ ካህን አኮ ማርያምሃ ዘይቄድስ አላ ውእቱ ይትቄደስ - ይህን ቅዳሴ የሚቀድስ ካህን ማርያምን የሚቀድሳት አይደለም ራሱ ይቀደሳል እንጂ” የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ከጥቅማቸው ከፍታ አንፃር ካየነው ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርብ ምሥጋና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ራሱን የቻለ ሰፊ ሐሳብ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው አይሆንም፡፡ ይልቁን ከሰዎች ጋር ባለን ማኅበራዊ ሕይወት ስለሚያጋጥሙንና ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ ምስጋናዎች በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሠዎች ምስጋና እንደሚገባቸው በቅዱስ ዳዊት የመዝሙር መጽሐፍ “ወለራትዓን ይደልዎሙ ክብር - ለቅኖችም ምስጋና ይገባቸዋል  መዝ 33:1 ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ልጁ ሰሎሞን ደግሞ መልካም ስለምትሠራ ልባም ሴት በጻፈበት የምሳሌ ክፍል  ልጆችዋ ይነሣሉ ምስጋናዋንም ይናገራሉ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል።መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።”  ምሳ 31:28 በማለት ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች መልካም ለሚሠሩ ሁሉ ምስጋና የሚገባ መሆኑን ብንረዳም ጎን ለጎን ልናደርጋቸው የሚገቡ በቂ ጥንቃቄዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-

፩- በመጠንና በተገባ ነገር ማመስገን

ምስጋናው ያልተመጠነና የተጋነነ ከሆነ በአንድ በኩል ተመስጋኙ በደንብ አንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ በምስጋናው እየተደሰተ ተዘናግቶ እንዲኖር የሚያደርገው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በውዳሴ ከንቱ እንዲወድቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አመስጋኙም ለውድቀት ምክንያት በመሆኑ ከመቀጣት አይድንም፡፡

፪-ከጕሕሉት(ከሽንገላ) እና ከውሸት የፀዳ መሆን

ብዙ ሰዎች ዘመን የወለደውን ንጉስ የወደደውን ተከትለው በልባቸው ባያምኑበት እንኳ መስሎ ለማደር ብለው ሰዎችን ያመሰግናሉ፡፡ ተመስጋኙ ይህ ከልብ ነው፣ ይህ አይደለም ብሎ መለየት ባይችልም ልብና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ ይፈርድብኛል ብለን

“በአፉሆሙ ይድህሩ ወበልቦሙ ይረግሙ - በአፋቸው ይመርቃሉ በልባቸውም ይረግማሉ፡፡” መዝ 62:4 ከተባሉት እንዳንቆጠር መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

፫ ምስጋናን ሱስ እስኪሆን አለማስለመድ

ምስጋና ከተለመደ እንደሌሎቹ ልማዶች ሱስ ሊሆን ይችላል፡፡ አበው “ኀዲገ ልማድ ፅኑዕ ውእቱ - ልማድን መተው ከባድ ነው” እንዳሉ በውዳሴ ሱስ የተጠመደ ሰውም ከዚህ ልማድ መውጣት ሊከብደው ሲቀር ቅር ሊሰኝ አልፎም ለምን አልተመሰገንኩም ብሎ ሊቆጣ ይችላል፡፡ ሰው እንዲህ ካለ ክፉና አስተቺ ልማድ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆን ከባድ ፍርድ ያለበት በመሆኑ ሱስ እስኪሆንበት በነጋ ጠባ ሰውን ከማመስገን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ምስጋናው ለማይገባቸውና የእነርሱ ባልሆነ ነገር ሰዎችን ማመስገን ጠቃሚ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ እንዳለም ተጽፏል፡፡ በሥጋዊ ትምህርት ጎበዝ ያልሆነውን ተማሪ ጎበዝ በማለት ተነሳሽነቱ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚቻል በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያልበረታን ሰውንም በማመስገን ማበርታት እንዲሁ ይጠቅማል፡፡ ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ መነኮሳት ላይ “ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ሎቱ ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ድልወቱ እስመ ወድሶ ለሰብእ ይወስክ ኃይለ - ሰውን የእርሱ ባልሆነና ባልተገባው ነገር አመስግነው ምስጋና ለሰው ኃይልን ይጨምራልና” ተብሎ ተጽፏል፡፡

     ከላይ ስለተገለጡት ተገቢ ምክንያቶች ማመስገን በዚህ ጽሑፍ ተነግረው የማያልቁ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ “ብፁዕ ሕዝብ ዘየአምር የብቦ - እልልታን (ምስጋናን) የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፡፡” መዝ 89:15 ተብሎ እንደተጻፈ ሰዎችን ለማመስገን መነሳት በራሱ የሚያስመሰግን ደግ ተግባር ነው፡፡ ቁጣው የራቀ ምሕረቱ የበዛ አምላክ “በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ማቴ 5:22
ብሎ ካስተማረን ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ሽልማት ይገባው ይሆን? “ዘይፀርፍ ላዕለ እኁኁ ዘረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል - በወንድሙ ላይ የተሳደበ በእግዚአብሔር ላይ ተሳደበ” ተብሎ ከተጻፈ ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ክብር ይጠብቀው ይሆን?
                                                                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

No comments:

Post a Comment