Friday, August 5, 2011

ውዳሴ ከንቱ (ክፍል ሁለት)

የሚጠቅም ውዳሴ (ውዳሴ ዘይረብሕ)

ውድ አንባቢያን ባለፈው ጽሑፋችን ስለ ውዳሴ ከንቱ በጥቂቱ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡  በፅሑፉ ፍፃሜ “በሌላ ጊዜ ስለሚገባ ውዳሴ እናቀርባለን” ብለን በገባነው ቃል መሠረት ዛሬ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ጎጂነቱን አውቃ የከለከለችው ከንቱ ምስጋና እንዳለ ሁሉ ተገቢ ነው ይጠቅማል ብላ የፈቀደችው ያዘዘችውም የምስጋና ዓይነት አለ፡፡ ይህ የምስጋና አይነት የተለየ ስያሜ  ባይኖረውም  ከውጤቱ በመነሳት ውዳሴ ዘይረብሕ (የሚረባ-ረብ ያለው ውዳሴ)፣ ውዳሴ ዘይበቊዕ (የሚጠቅም ውዳሴ) ልንለው እንችላለን፡፡

ለአምላካችን እግዚአብሔር፤ለቅዱሳን፤ በሥራቸው ሊመሰገኑ ለሚገባቸው ቅን ሰዎች፤ አንዳንዴም በምስጋና ልናበረታቸው ለሚገቡ ድኩማን የሚደረጉ ምስጋናዎች ከዚህ ዓይነቱ ምስጋና ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡

ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርቡ ምስጋናዎች አመስጋኙን ብቻ ሲጠቅሙ የቀሩት ደግሞ የሚጠቅሙበት ጎዳና ቢለያይም አመስጋኙንም ተመስጋኙንም የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ምስጋና አመስጋኙን ብቻ ሊጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ በቅዳሴ ማርያም ላይ “ዘንተ ቅዳሴ ዘይቄድስ ካህን አኮ ማርያምሃ ዘይቄድስ አላ ውእቱ ይትቄደስ - ይህን ቅዳሴ የሚቀድስ ካህን ማርያምን የሚቀድሳት አይደለም ራሱ ይቀደሳል እንጂ” የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ከጥቅማቸው ከፍታ አንፃር ካየነው ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን የሚቀርብ ምሥጋና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ራሱን የቻለ ሰፊ ሐሳብ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው አይሆንም፡፡ ይልቁን ከሰዎች ጋር ባለን ማኅበራዊ ሕይወት ስለሚያጋጥሙንና ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ ምስጋናዎች በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሠዎች ምስጋና እንደሚገባቸው በቅዱስ ዳዊት የመዝሙር መጽሐፍ “ወለራትዓን ይደልዎሙ ክብር - ለቅኖችም ምስጋና ይገባቸዋል  መዝ 33:1 ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ልጁ ሰሎሞን ደግሞ መልካም ስለምትሠራ ልባም ሴት በጻፈበት የምሳሌ ክፍል  ልጆችዋ ይነሣሉ ምስጋናዋንም ይናገራሉ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል።መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።”  ምሳ 31:28 በማለት ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች መልካም ለሚሠሩ ሁሉ ምስጋና የሚገባ መሆኑን ብንረዳም ጎን ለጎን ልናደርጋቸው የሚገቡ በቂ ጥንቃቄዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-

፩- በመጠንና በተገባ ነገር ማመስገን

ምስጋናው ያልተመጠነና የተጋነነ ከሆነ በአንድ በኩል ተመስጋኙ በደንብ አንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ በምስጋናው እየተደሰተ ተዘናግቶ እንዲኖር የሚያደርገው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በውዳሴ ከንቱ እንዲወድቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አመስጋኙም ለውድቀት ምክንያት በመሆኑ ከመቀጣት አይድንም፡፡

፪-ከጕሕሉት(ከሽንገላ) እና ከውሸት የፀዳ መሆን

ብዙ ሰዎች ዘመን የወለደውን ንጉስ የወደደውን ተከትለው በልባቸው ባያምኑበት እንኳ መስሎ ለማደር ብለው ሰዎችን ያመሰግናሉ፡፡ ተመስጋኙ ይህ ከልብ ነው፣ ይህ አይደለም ብሎ መለየት ባይችልም ልብና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ ይፈርድብኛል ብለን

“በአፉሆሙ ይድህሩ ወበልቦሙ ይረግሙ - በአፋቸው ይመርቃሉ በልባቸውም ይረግማሉ፡፡” መዝ 62:4 ከተባሉት እንዳንቆጠር መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

፫ ምስጋናን ሱስ እስኪሆን አለማስለመድ

ምስጋና ከተለመደ እንደሌሎቹ ልማዶች ሱስ ሊሆን ይችላል፡፡ አበው “ኀዲገ ልማድ ፅኑዕ ውእቱ - ልማድን መተው ከባድ ነው” እንዳሉ በውዳሴ ሱስ የተጠመደ ሰውም ከዚህ ልማድ መውጣት ሊከብደው ሲቀር ቅር ሊሰኝ አልፎም ለምን አልተመሰገንኩም ብሎ ሊቆጣ ይችላል፡፡ ሰው እንዲህ ካለ ክፉና አስተቺ ልማድ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆን ከባድ ፍርድ ያለበት በመሆኑ ሱስ እስኪሆንበት በነጋ ጠባ ሰውን ከማመስገን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት መልካም ለሚሠሩና ቅን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ምስጋናው ለማይገባቸውና የእነርሱ ባልሆነ ነገር ሰዎችን ማመስገን ጠቃሚ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ እንዳለም ተጽፏል፡፡ በሥጋዊ ትምህርት ጎበዝ ያልሆነውን ተማሪ ጎበዝ በማለት ተነሳሽነቱ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚቻል በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያልበረታን ሰውንም በማመስገን ማበርታት እንዲሁ ይጠቅማል፡፡ ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ መነኮሳት ላይ “ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ሎቱ ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ድልወቱ እስመ ወድሶ ለሰብእ ይወስክ ኃይለ - ሰውን የእርሱ ባልሆነና ባልተገባው ነገር አመስግነው ምስጋና ለሰው ኃይልን ይጨምራልና” ተብሎ ተጽፏል፡፡

     ከላይ ስለተገለጡት ተገቢ ምክንያቶች ማመስገን በዚህ ጽሑፍ ተነግረው የማያልቁ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ “ብፁዕ ሕዝብ ዘየአምር የብቦ - እልልታን (ምስጋናን) የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፡፡” መዝ 89:15 ተብሎ እንደተጻፈ ሰዎችን ለማመስገን መነሳት በራሱ የሚያስመሰግን ደግ ተግባር ነው፡፡ ቁጣው የራቀ ምሕረቱ የበዛ አምላክ “በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ማቴ 5:22
ብሎ ካስተማረን ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ሽልማት ይገባው ይሆን? “ዘይፀርፍ ላዕለ እኁኁ ዘረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል - በወንድሙ ላይ የተሳደበ በእግዚአብሔር ላይ ተሳደበ” ተብሎ ከተጻፈ ወንድሙን ያመሰገነ ምን ይነት ክብር ይጠብቀው ይሆን?
                                                                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Thursday, August 4, 2011

ስለ ተዋህዶ

ከ፫ቱ አካላት  ፩ዱ አካል ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ ፶፻፭፻ (5500) ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሁኖ ተወለደ፡፡ መለኮት ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት እንበለ ውላጤ፣ እንበለ ቱሳሔ፣ እንበለ ቡአዴ፣ እንበለ ምንታዌ ፩ አካል ፩ ባሕርይ ሆነ  " ፩ ውእቱ እምቅድመ ይሠጎ ወ፩ ውእቱ እምድኅረ ተሠገወ "  ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ሰውም ከሆነ በኋላ ባሕርዩ  ፩ ነው "  አንዳለ ቄርሎስ፡፡ ጎርጎርዮስም  " ውእቱ እግዚአብሔር ዘኮነ ሰብአ ወውእቱ ሰብእ ዘኮነ አምላክ በተዋህዶተ መለኮት "   "በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ አምላክም የሆነ ሰው እሱ ብቻ ነው" ብሏል፡፡  ሥጋም በተዋህዶተ ቃል እንደከበረ ምስክር ዮሐንስ አፈወርቅ  " ወኢረሰየ ሎቱ ህፀተ ሶበ ኮነ ልብሰ አባሎ ወዳዕሙ ሥጋ ረብሀ ስብሐተ ሶበ ኮነ ልብሶ ለፈጣረ" ብሏል "በሥጋ የነበረ ንዴት በተዋህዶተ ቃል ጠፋ የቃል ክብር ለሥጋ በተዋህዶ ገንዘቡ ሆነ"  ብሏል፡፡

     ተዋህዶ ሃማኖት ሳይማሩ በድፍረት ልመርምርህ ሲሉት የማይመረመር የተሠወረ ነው፡፡ ወጥቶ ወርዶ ተምሮ በፍቅር በትህትና በግብረ ገብነት ሁኖ ሲመረምሩት ግን እንደ ፀሐይ የበራ ነው፡፡ የሃይማትን ትምህርት መማር አዋቂ ነኝ ለማለት፣ ራስን ለማግነን፣ ሰውን ለመንቀፍ፣ ውሳጣዊ ዕውቀት ሳይኖር በዝምተኝነት አዋቂ መስሎ በመታየት አይደለም፡፡ በሥጋየ ምን ፈተና ይገጥመኝ ይሆን ? በነፍሴስ ምን ዕንቅፋት ይቆየኝ ይሆን እያሉ በማዘን በመጸለይ ስለኛ ቤዛ ሆኖ የሞተልን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማሙን ሞቱን ለማስታወስና እሱን ለመከተል ነው እንጂ፡፡

     ከ፫ቱ አካላት ፩ዱ አካል ወልድ እኛን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ለማዳን ስለኛ ሰውም ሆኖ በሥጋ ተወለደ ባልን ጊዜ ፪ት ልደት እንዳለ እናምናለን፡፡ መጀመሪያ ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው ፪ኛም    ፭ሺህ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከተወለደም በኋላ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ እየሠራ አደገ ፡፡ በዚህ ዓለም "፫ ዓመት ከ፫ ወር አስተምሮ ስለእኛ የሞት ፍርድን ተቀብሎ በመስቀል ተስቅሎ ሞተ፡፡ በሞቱም ዓለምን አድኖ ፫ መዓልት ፫ ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ፡፡ ከተነሣም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እየታየ ጉባኤ ሠርቶም መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማረ በምድር ላይ ፵ ቀን ከቆየ በኋላ በመላእክት ምስጋና በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱ ቀኝ (ዕሪና) ተቀመጠ መላእክት ተገዙለት ፩ኛ ጴጥ ፫፡፳፪፡፡ ዳግመኛ መጥቶ ሰማይና ምድርን ያሳልፋል ለጻድቃን ይፈርዳላቸዋል በኃጥአንም ይፈርድባቸዋል  ማቴ ፳፭፡፴፩፡፡ ክርስቶስ ቃለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ድንግል ማርያምንም በአማን ወላዲተ አምላክ ወላዲተ ቃል ብሎ ማመን ነው ፡፡ እንዲህ ካልሆነ ተዋህዶ ማለት አይገኝም ፡፡ እርሱም ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሰማይ የወጣ የለም ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር እርሱም በሰማይ የሚኖር ነው፡፡ ዮሐ ፫ ፡፲፫ በማለቱ ፩ አካል ፩ ባህርይ መሆኑን አስረድቶናል፡፡
                                                           ይቆየን!

Friday, July 22, 2011

ቅዱሳን መላእክት

   መላእክት የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ክፍል እና ምዕራፍ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን በእነዚህ የተጠቀሱት ክፍሎች ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉ ቅዱሳን መላእክትን ይመለከታሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ መላእክት የሚለውን ስም መጽሐፍ ቅዱስ እንደየ አገባቡ ለሦስት ነገሮች ሲጠቀምበት እንመለከታለን፡፡ 

. አለቆች፣ገዢዎች ሲል

          መልአክ የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲሆን ገዢ፣አስተዳዳሪ፣አለቃየሚል ፍቺን ይሰጣል፡፡ይኸውም በዮሐ 3፥1 ላይ ምስጢረ ጥምቀትን እንደሚገባ አድርጎ ስላስተማረው ስለ አይሁድ አለቃ ኒቆዲሞስ ሲናገር በግዕዙ ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እም ፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ መልአኮሙ ለአይሁድበማለት ሲገልጸው የአማርኛ አቻ ትርጉሙም ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆን ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል የአይሁድ አለቃየሚል ነው፡፡ስለዚህ በዚህ ክፍል ላይ መላእክት ተብሎ መጠቀሱ ገዢን አለቅነትን ለማመልከት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በተጨማሪም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን በማመናቸው እና በመከተላቸው እርሱና ሐዋርያቱ ለሰዎች እንዲሁም ለሹማምንት መጫወቻ እና መዘባበቻ እንደሆኑ ሲናገር ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልናበማለት ገልጾታል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋልና ማጤን ያለብን ነገር ቢኖር መላእክት ብሎ የጠቀሰው የምድር ሹማምንትን እንጂ ፌዝ እና ስላቅ የሌለባቸው ንጹሐን መላእክትን እንዳልሆነ ነው፡፡ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ የቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎችንና አስተዳዳሪዎችን መላእክት በማለት ጠርቷቸዋል፡፡ (1 ቆሮ 4፥9 ፣ራእይ 1፥20) 

ለ. ሠራዊተ አጋንንትን

          ተፈጥሮአቸው እንደ መላእክት የሆነ ኋላ ግን በገዛ ፈቃዳቸው ከእግዚአብሔር ከአምላካቸው የተነጠሉ ከመንግስቱ የተለዩ ሠራዊተ አጋንንትን መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት በማለት ይጠራቸዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ዓላማቸውን ስለሳቱትና ክብራቸውን ስለተነፈጉት ሠራዊተ አጋንንት እስከ ምፅአተ ክርስቶስ ድረስ ከጨለማ በታች ሆነው በእስራት እንደሚቆዩ ሲናገር መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋልብሏል፡፡ኢዮብም አምላክነትን ሽቶ ፈጣሪውን ክዶ በተዋረደና በስንፍና መረብ በተጠላለፈ ሰይጣንና ሠራዊቱ እግዚአብሔር እንደ ማይተማመን ሲገልጽ እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም  መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋልነገር ግን ይህቺን ጥቅስ በመያዝ ትጉሃን የሆኑ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ቅዱሳን መላእክትን ለመንቀፍ የሚጣጣሩ መናፍቃን አሉ፡፡ እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ያቀለዋል!ምንም የስም አጠራራቸውን ሊያጠፉ ቢጥሩም ከምንም በላይ ግን ቅዱሳን መላእክት ስማቸው በእግዚአብሔር ፊት የሰለጠነ ነው!፡፡ (ያዕ 1፥6 ፣ ኢዮ 4፥18) 

. ቅዱሳን መላእክት

መላእክት የሚለው ቃል በሌላ አገባብ ለአከከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን መልእክተኛ ፣ ተላላኪ የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡ ይህንንም የአገባብ ትርጉም የምንጠቀመው ለቅዱሳን መላእክት ብቻ ሲሆን ነው፡፡ ይህንን ትርጉም በመጠቀም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ቅዱሳን መላእክትን ተጠቅሰው እናያለን፡፡ ለአብነት ያህልም አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ባያት ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርስ መሰላል ላይ ሲወጡና ሲወርዱ የነበሩትን መላእክት ከላይ ከጠቀስናቸው የአገባብ ትርጉሞች ውጪ መሆኑን ሲያመለክተን  የእግዚአብሔር መላእክትበማለት ጠርቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ         ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል›› በማለት ከሠራዊተ አጋንንት እና ለገዢዎች ከሚሰጠው ትርጉም በተለየ መልኩ ከትቦታል፡፡(ዘፍ.28፥12፣ ዘፍ. 32፥1፣ መዝ 33፥7፣ዕብ 1፥6)
በአጠቃላይ መላእክትየሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት አይነት የአገባብ ፍቺ እንዳለው ካወቅን ይህ ጽሑፋችንም የሚያተኩረው በቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮ እና አገልግሎት ላይ ይሆናል፡፡ ቅዱሳን መላእክት የተፈጠሩት በእለተ እሁድ ሲሆን ስለተፈጥሯቸውም በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ሁለት አይነት ሐሳብ አለ፡፡
የመጀመሪያው ሐሳብ ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረዋል የሚል ሲሆን እንደ ማስረጃነትም የሚያቀርቡት በመጽሐፈ መቃብያን የተጠቀሰውን ‹‹ ወሶበ ኢያዕኮትኮ ለዘፈጠረከ እምነፋስ ወነድ ›› ‹‹ ረቂቅ የምትሆን አንተ ከእሳትና ከነፋስ የፈጠረህን አላመሰግንም ባልክ ጊዜ…›› የሚለውን እና በዳዊት መዝሙር ላይ የተጠቀሰውን ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ ወለእለ ይትለአክዎ ነደ እሳት›› ‹‹ መላእክቱን መንፈስ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ›› የሚሉት ይካተቱበታል፡፡ መዝ. 103፥4፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከእሳትና ከነፋስ አልተፈጠሩም የሚሉት ሲሆኑ እነዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ ‹‹ሶበሰ ተፈጥሩ እምነፋስ ወነድ እሞቱ ወእማሰኑ ከማነ›› ‹እነሱስ ከእሳትና ከነፋስ ተፈጥረው ቢሆን እንደኛ ታማሚ ሟች በሆኑ ነበር›› የሚለውን በመጽሐፈ አክሲማሮስ ላይ የተጠቀሰውን በመመርኮዝ ነው፡፡ ሁለቱን  ሲያስታርቁት ግን ከእሳትና ከነፋስ ተፈጠሩ ማለቱ በግብር (በስራ) ስለሚመስሉት ነው፡፡ ይኸውም እሳት ረቂቅ እንደሆነ መላእክትም ረቂቃን ናቸው፤ እሳት ኃያል ነው መላእክትም ኃያላን ናቸው፤ እሳት ብሩህ እንደሆነ መላእክትም ብሩሃነ አእምሮ መሆናቸውን ሲያመለክት፤ ከነፋስ ተፈጠሩ ማለቱም ነፋስ ፈጣን እንደሆነ እነርሱም ለተልእኮ ፈጣን መሆናቸውን ለማመልከት እንጂ ተፈጥሯቸውስ ‹‹እምኀበ አልቦ ኀበቦ›› ‹‹እምኀበ ኢምንት ኀበ ምንት›› ካለመኖር ወደ መኖር ነው፡፡

የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ለነገረ ቅዱሳን ካላት ታላቅ አክብሮትና ፍቅር የተነሳ እንኳን ሥራቸውንና ትምህርታቸውን ቀርቶ ስማቸውንም በፊደል ለይታ ልዩ በሆነ ምስጢርና አንድምታዊ ትርጉም አሰባጥራ ለልጆቿ ለምእመናን ታስተምራለች፡፡እኛም ይህን አብነት በማድረግ በዚች ጽሑፍ የመላእክትን ክብርና አገልግሎት ከስማቸው ፊደል ፍቺ ጋር አዋህደን ለማየት እንሞክራለን፡፡ 
ጋብያን

ከመላእክት አገልግሎትና ተልእኮ መካከል የሰውን ልጅ ለቁመተ ስጋ የሚሆን ምግብን መመገብ አንዱ ነው፡፡ይህም ሐሳብ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተከትቦ (ተጽፎ) እናገኘዋለን፡፡ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ፍቅረ ጣኦት ካናወዛት ከንግስት ኤልዛቤል ጋር ተጣልቶ በተሰደደ ጊዜ ድካም ተሰምቶት ከጥላ ስር አንቀላፍቶ ሳለ መልአከ እግዚአብርም የኤልያስን መራብና መጠማት ስላወቀ እንጀራን በአገልግል ውኃን በመንቀል አድርጎ መግቦት ነበር፡፡(መጽ.ነገ. ቀዳ 19፥2-8) ኅዳር አስራ ሁለት ቀን ቤተ ክርስቲያችን በታላቅ ድምቀት የምታከብረው የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓልም የሚያስታውሰን አርባ ዘመን ሙሉ በበረሀ ሲገዙ ለነበሩ ሕዝበ እስራኤል መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል መናን ከሰማይ እያወረደ እንደመገባቸውና እስከ ስደታቸው ፍጻሜ በመግቦቱ እንዳልተለያቸው ነው(ዘጸ 16፥35)፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ስለ መላእክት መጋቢነት ሲነገር የሚደንቃቸውና ግራ የሚያጋባቸው አሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ካለመረዳት የተነሳ ነው እንጂ እንኳን ንጹሐን የእግዚአብሔር አገልጋዮች መላእክት ቀርቶ ህጸጽ ጉድለት የሚገኝባቸው የሰው ልጆችም እንዲህ ያለውን ስራ እንደሰሩ በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን ፡፡ መላእክት ከምግበ ስጋ ባሻገር ምግበ ነፍስ የሆነውንም ጽድቅ ይመግቡናል (ያስተምሩናል) ፡፡ ( ራዕይ 18፥10  ዳን 10፥21)       

ዕላውያን

ይህም ማለት መላእክት ሰማያውያን እንደሆኑ የሚያስረዳን ቃል ነው፡፡ መላእክት ሰማያውያን መሆናቸውን ገባሬሆሙ ለመላእክት (የመላእክት ፈጣሪያቸው) የሆነ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር በሆነ ወንጌሉ ስለ መላእክት በጠቀሰበት ትምህርቱ  ‹‹የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ…›› ‹‹እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ…›› እና የመሳሰሉትን ተናግሯል፡፡ ላዕላውያን የሚለው ቃል ሰማያውያን ከሚለው ፍቺው በተጨማሪ በክብር ከፍ ያሉ ልዑላነ ክብር  የሚል ፍቺ ይኖረዋል፡፡ይህም ፍቺ በበለጠ ክቡራን ከሚለው ቃል ፍቺ ጋር ስለሚወራረስ በዚያ ስር ለማየት እንሞክራለን፡፡ (ማቴ. 24፥36 ማቴ. 22፥30) 
ቁባነ ምሕረት

የቃሉ ፍቺ በምሕረት የሚጠብቁ የሚል ሲሆን መላእክት ዑቃቤ (ጠባቂ) በመባል ይታወቃሉ፡፡ ለርዕሳችንም እንደ መግቢያ የተጠቀምነውም ‹‹በመንገድህም ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁት ቦታም ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ›› የሚለውም ቃል የሚጠቁመን መላእክት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላኩ ጠባቂዎቻችን መሆናቸውን ነው፡፡ የመላእክት አገልግሎት ሰውን መጠበቅ ከመከራ ከችግር ማዳን እንደሆነ ቅዱስ ጻውሎስ ሲናገር ‹‹ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለመርዳት የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን›› በማለት በተረዳ መልኩ አስቀምጦታል(ዕብ 1፥14)፡፡ታዲያ የመላእክትን ጠባቂነት አለማመን ከክህደት አልፎ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ፍጹም መንቀፍ የጻፉትንም ቅዱሳን ውሸታም ማለት እንደሆነ ማን በነገረን!? ያለ መላእክት ጠባቂነት የሰው ልጅ እንኳን አርባና ሃምሳ ዘመን ቀርቶ ለአንድ ማይክሮ ሰከንድ ያህል መሰንበት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የመላእክቱ ጥበቃ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና! የሚደንቀው ግን እንዲህ እያቃለልናቸውና እያጣጣልናቸው እኛን በትጋትና በትእግስት መጠበቃቸው ነው፡፡ በእውነት እንዲህ ላለ ትዕግስት አንክሮ ይገባል! እንደዚህም ላለው ጥበቃ ምስጋና ይገባል!
 
ቡራን
መላእክት ክቡራን ይባላሉ፡፡በንጽሕናውና በቅድስናው ከመላእክት ክብር ጋር የሚተካከል ክብር ያለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ የመላእክትን ክብር ሲናገር ‹‹ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ሲወርድ አየሁ ከክብሩም የተነሳ ምድር በራች›› በማለት ነበር የገለጸው ራዕይ 18፣1 ፡፡እንደዚሁም በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ መላእክት ክብር በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡ከነዚህም መካከል በዘጸ 22 ላይ የተጠቀሰው የበለዓምን ታሪክ ብቻ ጠቅሰን ስለ መላእክት ክብር ብዙ መነጋገር እንችላለን ነገር ግን ጊዜውም ወረቀቱም ስለሚገድበን በአጭሩ እንመለከተዋለን፡፡በለዓም ምንም ዓይነ ልቡናው ቢታወርበትም ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ መልአኩ በተገለጸለት ጊዜ ከክብሩ የተነሳ በግንባሩ ተደፍቶ እንደሰገደለት እናመለከታለን፡፡ ስለዚህ መላእክት ክቡራን ከመሆናቸውም በላይ ለክብራቸው ከጉልበት በርከክ ብሎ በግንባር መሬት ነክቶ እጅ መንሳት እንደሚገባ ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተጨማሪ መላእክት ክቡራን ናቸው የምንለው በላያቸው ከሚያድርባቸው ከእግዚአብሔር የተነሳ ነው፡፡ አምላካችን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ባወጣቸው ጊዜ ይረዳቸውና ከመከራ ይታደጋቸው ዘንድ ስለ ላከው መልአክ ሕዝቡን ሲያስጠነቅቅ ‹‹ ስሜ በርሱ ነውና መልአኬን አታስመርሩት ›› በማለት የእርሱ ክብር በእነርሱ ላይ እንዳለ በተረዳ ነገር ተናግሮናል፡፡ ስለዚህ መላእክትን አለማክበር በእነርሱ የሚከብር እግዚአብሔርን አለማክበር ነው፡፡ ስማቸውን ጠርቶ ላለመማጸን ‹‹እነርሱ ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ብቻ የሚላኩ ተላላኪዎች ናቸው›› ማለት አያዋጣም፡፡ይልቁኑ ‹እግዚአብሔር ያከበረውን› ማቅለል ሰሪውንና አክባሪውን ተሳስተሃል አርም ማለት በመሆኑ የገሃነምን ፍርድ ሳያመጣ አይቀርም!!!ስለዚህ መላእክትን እግዚአብሔር ባከበራቸው ክብር ማክበር ይገባል፡፡

ጉሃን
ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደተናገረ መላእክት ሀያ አራት ሠዓት ሙሉ ያለማቋረጥ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል (ኢሳ 6)፡፡‹‹እስመ እረፍቶሙ አኮቴቶሙ እስመ አኮቴቶሙ እረፍቶሙ›› ‹‹እረፍታቸው ምስጋናቸው ምስጋናቸው እረፍታቸው›› እንዲል፡፡ ከዚህ ግብራቸው የተነሳ ቤተ ክርስቲያን ትጉሃን ብላ ትጠራቸዋለች፡፡       ት የሚለው ቃል ከትጉሃን በተጨማሪ ትሁታን ተብሎ ይፈታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሙሴ ስጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ ሰይጣን ባለው የስድብ አፍ ብዙ ጽርፈትን (ስድብን) በተናገረ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ግን እግዚአብሔር ይገስጽህ ከማለት ያለፈ ምንም አልተናገረውም ነበር፡፡ ይህንንም ያደረገው ስለ ስድቡ ሰይጣንን መቅጣት ሳይችል ወይም ስልጣኑ ሳይኖረው ቀርቶ ሳይሆን ስለ ትህትናው ታገሰው እንጂ፡፡(ይሁ 1፣6)       
በአጠቃላይ እስከአሁን የጠቀስናቸው ዝርዝር ሐሳቦች ስለ መላእክት ተፈጥሮ፣ስለ አገልግሎታቸው እንዲሁም ስለ ስማቸው ትርጉም መጠነኛ የሆነ የቤተ ክርስቲያን እውቀት እንደጨበጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ይቆየን!
ዲ. አቤል ካሳሁን

Thursday, July 21, 2011

ውዳሴ ከንቱ


ውዳሴ ከንቱ
 ውዳሴ ከንቱ የሚለው ቃል የማይረባ የማይጠቅም  ውዳሴ የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን  ውዳሴ  ብጡል (የተናቀ፤ ተርታ) ውዳሴ ተብሎም ይጠራል፡፡ የቃሉ ትርጉም  በዚህ መልኩ የሚፈታ  ይሁን እንጂየማይጠቅምከመሆን አልፎ  ሰውን ሊጎዳ የሚችል ነገር በመሆኑ  የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት  አጥብቀን   ልንሸሸው እንዲሚገባ ያስተምራሉ፡፡
  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩ ስር ተቀምጣ ቃላት ታዳምጥ የነበረችውን የማርታ እህት  ማርያምንማርያምስ የማይቀሟትን  በጎ ዕድል መረጠችሉቃ10÷42  ብሎ ያመሰገነበትን  ቃል አበው ሲተረጉሙመማር ውዳሴ ከንቱ  የለውም “  አላውቅም  ማለት ነውና፡፡  ስለዚህም  አጋንንት  የማይቀሟትን (ዋጋዋን ) የማያስቀሩባትን  መማርን መረጠች ማለት ነው ብለው መተርጎማቸው ‹‹ውዳሴ ከንቱ›› የሰውን የልፋት ዋጋ  በምድራዊ ክብር  የሚያስቀር  ከንቱ ነገር መሆኑን ያስረዳል፡፡  አበው ከውዳሴ ከንቱ  እንድንጠበቅ ማስተማራቸው  የመልካም ስራችን  ዋጋ  ሰዎች  በሚያቀርቡልን የምስጋና ስጦታ ምክንያት በምድር  እንዳይቀርብን በማሰብ ነው፡፡ በወንጌልም ጌታ ከሰዎች ምስጋና  በመሻት መልካም  ሥራቸውን  በሰው  ፊት ስላደረጉ ፈሪሳውያን  ሲናገር  “እሙንቱሰ ነሥኡ እሴቶሙእነዚህስ  ዋጋቸውን  ተቀብለዋልማቴ6÷2  በማለት ከሰው የተቀበሉት ምስጋና  ሰማያዊ  ዋጋቸውን እንዳሳጣቸው አስተምሯል፡፡
 እንዲህ ስንል ግን በሰው የተመሰገነ ሁሉ ውዳሴ ከንቱ  ሆኖበታል   ያልተመሰገነ ደግሞ አልሆነበትም  ማለትም  አይደለም፡፡  በልቦናው   የመመስገን መሻት  ኖሮት  መልካም ሥራ  የሠራ  ነገር ግን   በለስ ያልቀናው  ያልተመሰገነ ሰው ሊሰርቅ ሄዶ አጥር ፀንቶበት፣  ውሻ ጮሆበት፣ ጠባቂ ነቅቶበት  የተመለሰ ሰውን  ይመስላል፡፡   መሻቱ  በልቦናው  ስላለ ሰዎች  ባያመሰግኑትም  ቅሉ ለመመስገን  በመሻት አስቀድሞ  ወድቋልና  ከሰው ውዳሴ  ሳይፈልግ  የሠራ ሰውም  ሰው ቢያመሰግነው  እንኳ አይሻውምና  በውዳሴ ከንቱ ወደቀ አያሰኝም፡፡  ይህም ውዳሴ ከንቱ ኃይል አግኝቶ ሰውን የሚጥለው  የተዘጋጀ ልቦና ሲኖረው መሆኑን  እንገነዘባለን ፡፡
 ውዳሴ ከንቱ  በሦስት ዓይነት  መንገድ ሲቀርብ እንደ  አቀራረቡና አቀባበሉም ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡
 .  ሰዎች ስለ እኛ
  ውዳሴ ከሰዎች ለእኛ በሚቀርብበት ወቅት  የሚያመሰግነን ሰው ማን ነው? ምስጋናውስ ለእኛ የሚገባን  ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች  ራሳችንን  መጠየቅ ከጉዳት  ይጠብቀናል ፡፡ የሚያመሰግነን  ሰው ማነው? የሚለውን ማሰባችን  ተወዳጅነትን  ለማትረፍና በአፀፋ ለመመስገን  ከሚመጡ ሰዎች  ሲጠብቀን ምስጋናው ለእኔ ይገባልን? የሚለውን ማሰብ ደግሞ ምስጋናውን ይገባናል ብሎ ከመቀበል ይጠብቀናል፡፡ በወንጌል ጌታችንቸር መምህር ሆይብሎ የቀረበው ሰው  መመስገንንና  ተወዳጅነትን ለማትረፍ  ሲሉ ምስጋና   ከሚያቀርቡ ሰዎች የሚመደብ ነው፡፡(ማር 10÷17) ምስጋናንለእኔ የሚገባ ነውን?” ብሎ መርምሮ መቀበልን የተማርነው ከቅዱሳን እናቶቻችንና ከቅዱሳን አባቶቻችን ነው፡፡

ክብር ይግባትና በሚገባት ግብር የተመሰገነች እመቤታችንእፎኑ ከመ ዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ - እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንዴት ይቀበሉታል?” ሉቃ 1÷29 ማለቷ ቅዱሳን በሚገባቸው ገንዘብ ቢመሰገኑ እንኳ (በትህትና) አይገባንም እንደሚሉ የሚያስረዳ ነው፡፡
በትንሣኤ ዘጉባኤምተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና ….” ተብለው የሚመሰገኑ ቅዱሳንመቼ ተርበህ አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አጠጣንህ?.....” ሲሉ ሠርተው እንዳልሰሩ ሆነው በትህትና እንዲመልሱ ተጽፏል፡፡ ማቴ 25÷44
አቡነ ተክለሃማኖትም ከብዙ ትሩፋትና ተጋድሎ በኋላአሌ ሊተ ወይ ሊተ ለዘኢገበርኩ ምንተ - ወዮ ለኔ ምንም ላልሠራሁትእያሉ ምርር ብለው ማልቀሳቸውን ገድላቸው ዘግቦታል፡፡
እኛም ምንም እንኳ ከእነርሱ መዐርገ ትህትና ደርሰን አይገባንም ማለት ባንችል በብሩህ ፊት ሆነን ውዳሴን እያጣጣሙ ከመቀበል መለየት ይገባናል፡፡ ይልቁንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዳሉት በምንመሰገንበት ወቅት የከፉ ኃጢአቶቻችንን እያሰብን ራሳችን መገሰፅ ይገባናል፡፡

. እኛ ስለሰዎች  
ምስጋና ከእኛ ስለ ሰዎች በሚቀርብበት ወቅትም ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ሰዎችን ማመስገንና እንዲመሰገኑ መፈለግ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ የበጎ ምግባር መገለጫ ነው፡፡
እንደ ዲያቢሎስ መመስገን ብቻ እንጂ ሰውን ማመስገንና ማበረታታት የማይፈልጉ ሰዎች አሉና፡፡ ነገር ግን የምስጋናውን ልክ የምናልፍ ከሆነ ለተመስጋኙ ጥቅም ከመሆን ይልቅ ፈተና የምንሆንበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡ በውዳሴ ከንቱ የወደቀ ከሆነም መሰናክል የሆንነው እኛ በመሆናችን እንቀጣለን፡፡
ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ቢኖር የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ከጥልቅ ቢጣል ይሻለው ነበርተብሎ ተጽፏልና፡፡ ማቴ 18÷6 ስለዚህም መመስገን የሚገባውን ሰው መለየትና መመስገን በሚገባው ልክ ማመስገን ከእኛ የሚጠበቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ደግሞምከጠላት መሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላልተብሎ እንደተፃፈ ለሰዎች ከሚቀርብላቸው ምስጋና ይልቅ ወቀሳና ምክር ለመሻሻል ይጠቅማቸዋልና ማመስገን ብቻ ሣይሆን መውቀስና መምከር ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን የአይሁድ መምህር የሆነ ኒቆዲሞስንአንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ብሎ አለማወቁን ገስፆ መምህርነቱን አመስግኖ እንደተናገረው የሐ 3÷10

. እኛ ስለ እኛ
 ውዳሴ ከንቱ ሰዎች እኛን በሚያመሰግኑበት ወቅት ባለን አቀባበል ወይም እኛ ለሰዎች በምናቀርበው ምስጋና ልክ ብቻ የሚመዘን አይደለም፡፡ እኛ ስለራሳችን ባለን አስተያየትና በምናቀርበው ምስጋናም ጭምር እንጂ፡፡በእርግጥ ለራስ ጥሩ አመለካከት መያዝና ራስን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ልክ ከሌለው ግን ለራሳችን ብቻ የምናዜም በውይይት መሃል እኛ ብቻ መነሳት የምንፈልግ ከእኛ ይልቅ ሌላ ሰው ቢነሣ ቅር የሚለን ገፍተንም ስለ ራሳችን ጥሩነት የምናወራ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፍየሌላ ሰው አፍ ያመስግንህተብሎ መጻፉ ሰው በራሱ አንደበት መመስገን እንደሌለበት የሚያስረዳ ነው፡፡ በወንጌልም የታዘዙትን ሁሉ በፈፀሙ ጊዜ አገልጋዮች ምን ማለት እንዳለባቸው የተቀመጠላቸው ትዕዛዝ  “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ”  የሚል ነው ሉቃ. 1710 ፡፡ ይህም ሰው ከልክ አልፎ ለራሱ ቦታ እንዳይሰጥና በውዳሴ ከንቱ  እንዳይወድቅ ለመጠበቅ  የታዘዘ ነው ፡፡ እራሳችን  ውዳሴ ከንቱ በመሆኑ  በማይጠቅም  ውዳሴ ላይ ብቻ አተኮረን  እንጂ ሚገቡና  የሚጠቀሙ የታዘዙም  ምስጋናዎች አሉ፡፡የማይጠቅም ውዳሴየሚለውን ርዕስ  በራሱ  የሚጠቅም ውዳሴ መኖሩን  የሚጠቁም  ነው፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድ የሚቀጥለውን ጽሑፍ ስለሚጠቅም ውዳሴ ይዘን እንቀርባለን፡፡
                                                                  ይቆየን                                                                                  
                                                                                              /  ተስፋሚካኤል አሰፋ